FM ADDIS 97.1(ኤፍ ኤም አዲስ 97.1) – Telegram
FM ADDIS 97.1(ኤፍ ኤም አዲስ 97.1)
8.5K subscribers
1.3K photos
37 videos
3 files
173 links
ይህ ትክክለኛ የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የቴሌግራም ቻናል ነው
Download Telegram
24 ሰዓት ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው የመገጭ  መስኖ ፕሮጀክት
***
መገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ያረፈበት ቦታ 870 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ 17 ሺህ ሔክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ይኖረዋል።

ከተጀመረ 15 ዓመታት ያስቆጠረው ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች እየተጓተተ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አልቻለም።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።

ፕሮጀክቱን በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ግንባታው በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ መሆኑን፣ ግንባታውን ካለፈው ዓመት ጀምሮ እያከናወነ የሚገኘው ሀገር በቀሉ ኮንትራክተር ቤአኤካ አስታውቋል።

በተለይም ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚረዱ መሰረታዊ የግንባታ ምዕራፎችን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉ ነው የተመላከተው።

አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ግንባታ 77 በመቶ መድረሱም ተጠቅሷል። ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅም ለ24 ሰዓት የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለጎንደር እና በጎንደር ዙሪያ ለሚገኙ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል።

በአባዲ ወይናይ
5
የጥበባትና ፈጠራ ኢንዱስትሪን ውጤታማነት ለማሳደግ የተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ
***

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ የጥበቡን ዘርፍ ተወዳዳሪነት እና ጠቀሜታ የሚያሳድግ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ መነሻ ሰነድ ላይ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ ፖሊሲው በተለይ ለጥበብ የፈጠራ ባለቤቶች ሕጋዊ ከለላ በመስጠት ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ የጥበብ ዘርፉን የሚደግፍ ፖሊሲ ባለመኖሩ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ አንስተዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ምሁራን እና ባለሙያዎችን በማሳተፍ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ መዘጋጀቱን አመላክተዋል። ይህም የመደመር መንግሥት ለጥበብ ዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል።

ከለውጡ በኋላ የመደመር መንግሥት ከኮሪደር ልማት ጎን ለጎን በርካታ የኪነ-ጥበብ ማዕከላትን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱንም ገልጸዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው የጥበብና የፈጠራ ኢንዱስትሪ ሃብቶችን በማጥናት፣ በመጠበቅ፣ በማልማትና ተደራሽ በማድረግ ለዘርፉ  ዕድገት እንዲውል የሚያስችል ነው ብለዋል። 

በቀጣይ ረቂቅ ፖሊሲውን የሚያዳብሩ የተለያዩ ግብዓቶች ከተሰበሰቡ በኋላ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ እንዲፀድቅ ይደረጋል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

ዘአማኑኤል መንግሥቱ
👍2
‎ግብርና ሚኒስቴር 258 መኪኖች እና 1 ሺህ 830 የሞተር ብስክሌቶችን ለክልሎች አበረከተ

***************

ግብርና ሚኒስቴር ለምግብ ሥርዓት ማጠናከርያ ፕሮግራም የሚሆኑ 258 መኪናዎችን እና 1 ሺህ 830 የሞተር ብስክሌቶችን ዛሬ ለክልሎች አስረክቧል።

‎ተሽከርካሪዎቹ በተለይም በገጠሩ አካባቢ ዝቅተኛ አቅም ያላቸው ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የምግብ ሥርዓት እንዲሻሻል የሚሰሩ ባለሙያዎችን እና የላቦራቶሪ ቁሶችን ለማጓጓዝ እንደሚውሉ በርክክቡ ወቅት ተገልጿል።

‎ሚኒስቴሩ ከዚህ በተጨማሪ የአየር ንብረትን ለሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ፕሮግራም 9 መኪኖች፣ 24 የሞተር ብስክሌቶች፣ የውኃ መሳቢያ ሞተር እንዲሁም 100 የመለዋወጫ ዕቃዎችን የያዙ ሳጥኖችን ለክልሎች አስረክቧል። ይህም በኢትዮጵያ የተጀመረውን የበጋ መስኖ ልማትን ይበልጥ ለማስፋፋት እንደሚያግዙ ነው የተገለፀው።

‎የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት፤ ለሁለቱም ፕሮግራሞች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው ድጋፍ ለክልሎች ተደርጓል። ‌‎ተሽከርካሪዎቹ ኢትዮጵያ የያዘችውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ለማሳካት አጋዥ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ድጋፉ ከልማት አጋሮች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደቀረበ ጠቁመዋል።‎

በባዬ ሙላት
😁1
አዲስ የጀመርነው መንገድ . . . !

የቀደመው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ ዋናው የኢኮኖሚው ዋልታ መንግስት ሆኖ የግሉ ዘርፍ እንደ ኪራይ ሰብሳቢ የሚቆጥር ሰለነበር አክሳሪ መንገድ ነበር፡፡ በመደመር መንግስት የግሉ ዘርፍ ካልተደገፈና ምቹና አሰሪ ምህዳር ተመቻችቶለት ከመንግስት ጋር በትብብር ጭምር መስራት ካልተቻለ የትም አይደረስም የሚል አቋም ተወስዶ እየተሰራበት ነው፡፡ ተስፋ ፈንጣቂ የምስራች ፍሬው ሲያፈራም እያየን ነው፡፡

አዎ! ህዝብና መንግስት ባይተባበሩ አረንጓዴ አሻራ በታየው ደረጃ ባልተሳካ ነበር፤ ታላቁ የህዳሴው ግድብ ለድል ባልበቃ ነበር፤ ህዝብ ፈቅዶ ባይተባበር ኖሮ የኮሪደር ልማታችን እንዲህ ባማረና አለምን ባስገረመ ፍጥነት ባልተሳካም ነበር፡፡ የመንግስት፣ የህዝብና የግል ባለሀብቱ ትብብር (Government public private partnership) ምን መስራት እንደሚያስችል እያየን ነው፡፡

ዛሬ ሀገር እስከ ሚቀይሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በትብብር የኢኮኖሚ ሞዴል እየተሰሩ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤት ልማት፣ በኮሪደር ልማት፣ በማእድን ልማት ለምሳሌ በቤኒሻንጉል የኩምሩክ ግዙፍ የወርቅ ማእድን ልማት፣ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር የጎዴ የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርክ፣ ቅሊንጦ ፋርም፣ የቴክኖሎጂ ፓርክ ግንባታና የመሳሰሉት በማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
1
የኢትዮጵያ ካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ቻይናን ከአውሮፓ ጋር በማገናኘት ዕውቅና አገኘ
***
የኢትዮጵያ ካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በቻይና እና አውሮፓ መካከል በሚደረገው የሎጂስቲክስ ግንኙነት ግንባታ ቁልፍ የሎጂስቲክስ አጋር በመባል ሽልማትን አገኘ።

አየር መንገዱ የቤልጂየም መንግሥት ከቻይና ሎጅስቲክስ ማኅበር ጋር በመሆን በቻይና ጓንዡ ባዘጋጀው ሥነ-ስርዓት ላይ ሽልማቱን ተቀብሏል።

አየር መንገዱ ዕውቅናውን ያገኘው፤ የተለያዩ ዕቃዎችን ከቻይና ወደ አውሮፓ በቤልጂየም በኩል በማጓጓዝ እንደ አገናኝ ድልድይ ሆኖ እየሰጠ ላለው ጠንካራ የካርጎ አገልግሎት ነው ተብሏል፡፡

በላሉ ኢታላ ነው
ለሰላም ሲባል ዩክሬን የኔቶ አባልነት ጥያቄዋን ትተዋለች፡- ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ
***

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም "ለሰላም ሲባል ዩክሬን የኔቶ አባልነት ጥያቄዋን ትተዋለች" ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ በአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከተመራው ልዑክ እና ከአውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በጀርመኗ ከተማ በርሊን እየመከሩ ነው፡፡

ውይይቱ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ያለመ ሲሆን ይህን ለማድረግ ያስችላል ተብሎ በተዘጋጀው የሰላም ስምምነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በፕሬዚዳንቷ ተወክላ ውይይት እያደረገች ያለችው ዩክሬን ለዘላቂ ሰላም መስፈን ቁርጠኛ መሆኗን አስታውቃለች፡፡

በዚህም ለጦርነቱ መባባስ አንዱ ምክንያት የነበረው የኔቶ አባልነት ጥያቄዋን በጊዜያዊነት መሰረዟን አስታውቃለች፡፡

በምላሹም ደህንነቷ እና ስምምነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ላይ ሀገራቱ ከጎኗ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርባለች፡፡

በተጨማሪም ከይዞታ ጋር የተያያዙ አለመስማማቶች ላይ ንግግሩ እንደሚካሄድ ነው የተጠቆመው፡፡

በአሜሪካ አስተባባሪነት እና በአውሮፓ ሀገራት ተሳትፎ የተዘጋጀው የሰላም ስምምነቱ ተኩስ አቁምን የመጀመሪያው ርምጃ በማድረግ የይዞታ ጥያቄዎችን፣ የደህንነት ዋስትና እንዲሁም የተጣሉ ማዕቀቦችን የሚዳስስ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ አስነብቧል፡፡

ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ከሩሲያ የተነሳ ሃሳብ ባይኖርም፣ በአውሮፓ ሀገራት በሚቃኝ ድርድር ላይ ሩሲያ የመገኘት ፍላጎት እንደሌላት ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡

በአፎሚያ ክበበው
1
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ያበለፀጋቸውን አዳዲስ ዲጂታል ፕላትፎርሞች ይፋ አደረገ
***
የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ያዘጋጀው 1ኛው የቱሪዝም ፎረም እየተካሄደ ነው።

ፎረሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር በይፋ ሲከፍቱ፤ መዲናዋ የዓለም የቱሪዝም መናገሻና መዳረሻ ትሆን ዘንድ የመደመር መንግሥት በቀጣይም በስፋት ሥራዎችን እንደሚያከናውን አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጥቂት ጊዜ ቢሆነውም ስብሰባዎችን እና ኮንፈረንሶችን መሠረት ካደረገውን የማይስ (MICE) ቱሪዝም በተጨማሪ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ቀርጾ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

አክለውም ኮሚሽኑ የቱሪዝም ዘርፉን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችሉ የተለያዩ ዲጂታል ፕላትፎርሞችን ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ማስጀመሩን ገልጸዋል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የቱሪዝም ንግድ አውደ ርዕይ እና የፎቶ ኤግዚቢሽን የቀረቡ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ከተማዋን ለማስተዋወቅ ያበለፀጋቸው ዲጂታል ፕላትፎርሞችም ይፋ ተደርገዋል።

ይፋ ከተደረጉትም ዲጂታል ፕላትፎርሞች መካከል 'ቪዝት አዲስ አበባ' የተሰኘው ፕላትፎርም በመዲናዋ የሚገኙ መዳረሻ ቦታዎችን ለጎብኚዎች የሚጠቁም እንዲሁም ሆቴል ያረፉ እንግዶችን ይበልጥ ለማገልገል የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

ፕላትፎርሞቹ በከተማዋ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችንና መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ እና የስፖርት ቱሪዝምን ለማጎልበት የሚያግዙ መሆናቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በአዲስ አበባ አራዳ ፓርክ እየተካሄደ የሚገኘው ፎረሙ ነገ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።

በሜሮን ምትኩ
2