Addis Standard Amharic – Telegram
Addis Standard Amharic
18K subscribers
4.66K photos
121 videos
3 files
3.71K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
#ሶማሊ ክልል #ጅግጅጋ ከተማ የተነሳው የእሳት አደጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሳይዛመት በቁጥጥር ስር ውሏል

በእሳት አደጋው ሳቢያ #932 ሱቆች ወድመዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ የተመራ ልዑክ ከፌዴራል እና ክልል ሃላፊዎች ጋር በመሆን ዛሬ ጠዋት የደረሰውን ውድመት ለመመልከት በቦታው ተገኝተዋል፡፡

ዛሬ ጠዋት ከጎረቤት #ሶማሊላንድ ዋና ከተማ #ሀርጌሳ ከንቲባ የተመራ የእሳት አደጋ አጥፊ ቡድን ወደ ስፍራው አምርቷል። ባለፈው አመት በሚያዝያ ወር በሀርጌሳ ከተማ #ዋሄን ገበያ ላይ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ በደረሰበት ወቅት የሶማሊ ክልል የነፍስ አድን ቡድን ወደ ስፍራው መላኩ ይታወሳል።

አዲሱ ታይዋን ተብሎ በሚጠራው የገበያ ማእከል ላይ የደረሰው የእሳት አደጋ መንስዔውእስካሁን አልታወቀም፡፡ በእሳት አደጋው ሳቢያ #932 ሱቆች ሲወድሙ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጧል። SRTV_Somali ያጋራው ምስል ከባድ ውድመት መድረሱን ያመላክታል፡፡
ዜና፡ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል ያሉ የማንነትና የወሰን ውዝግቦች በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈቱ እንቅስቃሴ መጀመሩን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ

ለ30 ዓመታት የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው አካባቢዎች ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ እንዲፈታና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የአማራ ክልል መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን የክልሉ የኮሙዩኒኬስን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ፡፡

የማንነትና የወሰን ጥያቄ ቢያንስ ከ30 አመታት በኋላ በህዝበ ውሳኔ እንዲፈጣ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ሕገ መንግስት ለማሻሻል ጥረቶች መጀመራቸውን አስታውሰው ጥያቄ ማቅረብ መቀጠላቸውንና በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱም ዝግጁነት ስለሚያስፈልግ ክልሉን ሰላም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡

አቶ ግዛቸው በነፃነት በመዘዋወር በተመለከተ በአንዳንድ አካባቢ ችግር መኖሩን ጠቅሰው የመንገድ መዘጋት፣ የመታገት አደጋዎች፣ ግድያ፣ ውድመትና ዘረፋ የክልሉን ሰላም በመደፍረስ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሱ ነው ብለዋል፡፡
https://rb.gy/ccnel
በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ ልዑካን ቡድን መቐለ ከተማ ገባ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ፓትርያርክ የሚመራ ልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል ከሚገኙ ብፁዓን አባቶች ጋር የሰላም ውይይት ለማድረግና የሰብዐዊ ድጋፍ ለማድረስ መቐለ ከተማ መግባቱን የ/ኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አስታወቀ።

ቀደም ሲል የተቋቋመው ኮሚቴው ወደ ክልሉ ከመጓዙ አስቀድሞ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ ልዑካን ቡድን ወደ መቐለ እንዲጓዝና የሰብዐዊ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በክልሉ ከሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ውይይት አድርጎ እንዲመለስ በቋሚ ሲኖዶስ መወሰኑና ይኸው በመቐለ ሊካሔድ የታሰበው መርሐ ግብርም አስቀድሞ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲደርስ ተደርጓል።

በዚህም መሰረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ ሐምሌ 3ቀን 2015 ዓ.ም ማለዳ ወደ ክልል ትግራይ መቐለ ከተማ አምርቷል።

ልዑካን ቡድኑ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመገኘት የሰብዐዊ ድጋፉን የሚያበረክት ሲሆን በክልሉ ጊዜያዊ መንግስት በኩል በሚመቻቸው መሠረት ተፈናቃይ ወገኖችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመርሐ ግብሩ መሰረትም ቅዱስ ፓትርያርኩና የልዑካን ቡድኑ አባላት በትግራይ ከሚገኙ ብፁዓን አባቶች ጋር ውይይት ያደርጋሉ።ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።
ዜና፡ #ለሱዳን ቀውስ እልባት ለማስገኘት #በአዲስ አበባ የኢጋድ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል፤ #ኤርትራ እንደማትሳተፍ ተገልጿል፤ ተመሳሳይ ጉባኤ #ካይሮ በተናጠል አዘጋጅታለች

በሱዳን የተከሰተውን ቀውስ በዲፕሎማሲ ለመፍታት በአዲስ አበባ የኢጋድ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ ኤርትራ እንደማትሳተፍ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ገልጸውልኛል ሲሉ የሱዳን ላዕለዋይ ምክር ቤት ምክትል ማሊክ #አጋር መናገራቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ድረገጽ ዘግቧል። የሱዳንን ግጭት ለመፍታት በአለም አቀፍም ይሁን በቀጠናው ሀገራት በኩል የሚቀርቡ ጥረቶች የፖለቲካ #ባዛሮች በመሆናቸው ኤርትራ በባዛሩ የመሳተፍ ፍላጎት የላትም ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ነግረውኛል ሲሉ ማሊክ አጋር መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል።

በሌላ ዜና በሳምንቱ አጋማሽ ተመሳሳይ ጉባኤ #ካይሮ በተናጠል ማዘጋጀቷን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
https://rb.gy/8i8zk
ዜና፡ #በትግራይ ጉብኝት እያካሄዱ የሚገኙት አቡነ #ማትያስ ከክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኙ፤ ግዜያዊ አስተዳደሩ በቤተክርስቲያኗ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ አቶ #ጌታቸው ገልጸዋል

በትግራይ ጉብኝት እያካሄዱ የሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተገለጸ።

ግዜያዊ አስተዳደሩ በቤተክርስቲያኗ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ አቶ ጌታቸው ረዳ እንደገለጹላቸው ከትግራይ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በትግራይ ክልል የሚገኙ አባቶች በምን ምክንያት በውይይቱ እንዳልተገኙ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸው የሆነ ሁኖ ግን መወያየት ጥሩ ነበረ፤ በመወያየት ሀሳብን መግለጽ ይቻላል፣ የደረሰውን ችግር መግለጹ ማስረዳቱ አንድ ቁምነገር ነው፤ ይሁንም አይሁንም ለማለት ውይይት ጥሩ ነበረ፤ የሆነ ሁኖ ከብጹአን አባቶች ጋር አልተገናኘንም ሲሉ ተደምጠዋል። ለወደፊቱ ለመገናኘት ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በትግራይ ከሚገኙ የቤተክርስቲያን አባቶች ጋር መወያየታቸውን በመድረኩ ላይ ያስታወቁት አቶ ጌታቸው እነሱን የማስገደድ ሃላፊነትም ስለጣንም ፍላጎቱም የለኝም ሲሉ ገልጸዋል።

https://rb.gy/sxh54
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚቀጥሉት 6 ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ እንዲሁም ተከራይ ማስወጣት የማይቻል መሆኑን አሳውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የኑሮ ውድነቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ የቤት ኪራይ ጭማሪ እንዳይደረግ በተለያዩ ተከታታይ ጊዜያት ውሳኔ ማሳለፉን አስተዳደሩ አስታውሷል፡፡

በቀጣይም በግል ከሚደረግ ስምምነት ውጪ ማንኛውም አከራይ ለሚቀጥሉት 6 ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ እንዲሁም ተከራይ ማስወጣት የማይቻል መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
ዜና፡ የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርሙ ኢጋድ ጠየቀ፤ የአባል ሀገራቱ ወታደሮችን በሱዳን ለማስፈርም ታስቧል

አዲስ አበባ በተካሄደው ስለሱዳን ጉዳይ በመከረው የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርሙ ተጠየቀ። ኢጋድ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ሁለቱም ሀይሎች ውጊያቸውን እንዲያቆሙና ባፋጣኝ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲፈጽሙ ጠይቋል።

በተመሳሳይ ኢጋድ በሱዳን የአባል ሀገራቱ ወታደሮች ወደ ሱዳን እንዲገቡ እና ንጹሃንን እንዲታደጉ ለማድረግ ሃሳብ ማቅረቡን ዘገባዎች አመላክተዋል። የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል ወደ ሱዳን እንዲገባ እና የሰብአዊ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተሰብስበው እንዲወስኑ ለማድረግ በአዲስ አበባ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከስምምነት መደረሱን ዘገባዎቹ አስታውቀዋል።

የሱዳን ወታደራዊ ሀይሎች በጉባኤው ላይ ባለመሳተፋቸው የተሰማውን ቅሬታ ኢጋድ በትላንትና መግለጫው አመላክቷል።

በሌላ ዜና የሱዳኑ ዳባንጋ ሬዲዮ ባሰራጨው ዘገባ ከኢጋዱ የአዲስ አበባ ጉባኤ ቀደም ብሎ ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሱዳን የሲቪል ፖለቲካ ሀይሎች ልዑካንን ተቀብለው ማነጋገራቸውን አስታውቋል።

https://rb.gy/qo2oi
በ2015 በጀት ዓመት 100 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 107 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

ከንቲባዋ በተሰበሰበው በገት በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ገንብተናል ብለዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት 140.29 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅደናል ያሉት ከንቲባዋ ይሄንን እቅድ ለማሳካት ግብር ከፋዮቻችንን ማበረታታት ተገቢ በመሆኑም ዛሬ የ2016 በጀት ዓመት ገቢ የማሰባሰብ ንቅናቄን አስጀምረናል ሲሉ ገልፀዋል።

የሰበሰብነውን ገንዘብ መልሰን ለዘላቂ ልማት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴውን በማነቃቃት የላቀ ሚና ለሚጫወቱ ፕሮጀክቶች በማዋልና የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል በታማኝነት እንሰራለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ዜና፡ አንድ እስራኤላዊ በጎንደር መታገቱን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5/2015 ዓ.ም፡- በዜግነት እስራኤላዊ የሆነ አንድ ግለሰብ በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በጎንደር ታግቶብኛል ሲል የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ። እስራኤላዊው የታገተው ማስለቀቂያ ገንዘብ በፈለጉ ሀይሎች መሆኑም ተጠቁሟል።

ታጋቹን እስራኤላዊ ለማስለቀቅ ዲፕሎማቶች ከአከባቢው የጸጥታ ሀይሎች እና ከኢንተርፖል ጋር በመቀናጀት እየሰሩ እንደሚገኙ መስሪያ ቤቱ ገልጿል። ታጋቹ እስራኤላዊ እድሜ በ70ዎቹ መሆኑን የጠቀሙት ዘገባዎች ወደ ጎንደር ያቀናው ከቀናት በፊት መሆኑን አስታውቀዋል።

ከአጋቾቹ ጋር ኢንተርፖል እና የአከባቢው የጸጥታ ሀይሎች ግንኙነት ለማድረግ መሞከራቸውን እና በወቅቱም ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቃቸውነ ዘገባዎቹ ጠቁመዋል። ለማስለቀቅ የተጠየቀው ገንዘብ በመጀመሪያ በሚሊዮኖች እንደነበረ አና ቆየት ብሎ በተደረገ ውይይት ወደ ሺዎች መውረዱን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች አመላክተዋል። ታጋቹ እስራኤላዊ በድምጽ ለቤተሰቦቹ በላከው መልዕክት እርዱኝ፣ በጫካ መሃል ላይ እገኛለሁ ማለቱን ያስነበቡት ዘገባዎቹ ዝናብ እየዘነበብኝ ነው እርዱኝ፤ እሁድ ዕለት መምጣት ነበረብኝ ግን መቆየቴ አይቀርም ይመስላል፤ ልጆቼ እርዱኝ፣ አሁን ያለሁበት ሁኔታን ለጠላቶቼም አልመኘውም ሲሉ እንደሚደመጡ አስታውቀዋል።

https://rb.gy/q2vgi
የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ በ99 የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

በደቡብ ክልል የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ በፖሊስ አመራር እና አባላት ላይ ሲያካሂድ በነበረው የግምገማ መድረክ፣ ከ96 በላይ የፖሊስ ማኔጅመንት እና አባላት ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

በፖሊስ አመራር እና አባላት ዘንድ የሚታዩ የአመለካከት፣ የአሰራር፣ የአመራር እና የሥነ-ምግባር ግድፈቶችን በማረም ለህብረተሰቡ ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ማበርከት የሚያስችል የግምገማ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ግምገማ ሂደት እንደተገባ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር ታረቀኝ አጥናፉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ በዞኑ ስር በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር የፖሊስ መዋቅር ሲያከናውን የነበረውን ዞናዊ የግምገማ መድረክ ሲያጠቃልል 70 የፖሊስ አባላት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ፤ 20 የፖሊስ አባላት ደግሞ ከኃላፊነታቸዉ እንዲነሱ የተወሰነ ሲሆን 6 የፖሊስ አባላት በዲስፕሊን እንዲጠየቁና 3 የፖሊስ አባላት ደግሞ ከሥራ ታግደው በህግ መጠየቅ አለባቸው እንዳለባቸው መባሉን ከደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።