Addis Standard Amharic – Telegram
Addis Standard Amharic
18K subscribers
4.75K photos
123 videos
3 files
3.78K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
ዜና: የዘንድሮ አመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ700 ሺህ በላይ ለሚሆኑ #ተማሪዎች በወረቀትና በኦላይን ይሰጣል ተባለ

የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከ700 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በወረቀትና በኦላይን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በድብልቅ (በወረቀትና በኦንላይን) ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረግ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ም/ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ገልጸዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዲጅታላይዜሽንና አይሲቲ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዘላለም አሰፋ በበኩላቸው ዘንድሮ ሀገሪቱ ካላት አቅም አንጻር በድብልቅ ፈተናውን ለመስጠት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደርጉን አንስተው በተለይም የኦንላይን ፈተናው በተመረጡ ከተሞች ብቻ እንደሚሰጥና ቅድመ ስልጠና እስከ ትምህርት ቤት ድርስ ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።

በኦንላይን ፈተናቸውን የሚወስዱ ተማሪዎችን ቴክኖሎጂውን እንዲያውቁት የተግባር ልምምድ ፈተናዎች በሶፍትዌሩ ተጭኖላቸው እንዲለማመዱና የስነልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ መደርጉን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

በተለይም የኔትዎርክ እና የመብራት መጠባበቂያ ጀኔሬተር የሌላቸው ተቋማት በፈተና ጣቢያነት እንደማይመረጡ የገለጹ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲዎችና ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ላሉ ተቋማት በክላስተር በማድረግ በፈተና ወቅት አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያዎች መመደባቸውንም አብራርተዋል።

ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ከሃምሌ 03/2016 ጀምሮ እንደሚሰጥ መግለጹ ይታወቃል።
ዜና: #በትግራይ ከሚገኙ ወጣቶች 81 በመቶ የሚሆኑት ስራአጥ መሆናቸውን እና 40 ከመቶዎቹ መሰደድ እንደሚፈልጉ አንድ ጥናት ጠቆመ

በትግራይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 81 ከመቶዎቹ ስራአጥ መሆናቸውና 40 ከመቶዎቹ መሰደድ እንደሚፈልጉ የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ያደረገው ጥናት ጠቆመ።

ጥናቱ እንደሚያሳየው በክልሉ ለሁለት ዓመት ከተደረገዉ ጦርነት በኋላ ያለዉ ሁኔታ ለወጣቶች ተስፋ አስቆራጭ ነዉ።

ከጦርነቱ በፊት በትግራይ የስራ አጥ ወጣቶች መጠን 30 ከመቶ እንደነበረ የጠቆመው ጥናቱ የደረሰው ውድመት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ምክንያቶች ተደምረው አሁን ላይ በትግራይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 81 ከመቶዎቹ ስራ አጥ መሆናቸውን አስታውቋል።

ስራ አጥ ከሆነው በተጨማሪ 89 ከመቶ የሚሆን በትግራይ የሚገኝ ወጣት ምንም ዓይነት ገቢ እንደሌለው የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ስራአስኪያጅ ሰናይ ከሓሰ መግለጻቸውን ከጀርመን ድምጽ የአማራኛ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ከፖለቲካ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ጥናቱ ባደረገው ዳሰሳ 66 ከመቶ የሚሆኑ የትግራይ ወጣቶች በፖለቲካ ጉዳዮች መሳተፍ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል ያሉት ስራ አስኪያጁ ይህም ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተስፋ ከማጣት የመነጨ ሊሆን ይችላል ሲሉ መላምታቸውን ማስቀመጣቸውን ዘገባው አመላክቷል።

በተለያየ መንገድ በፖለቲካዊ ጉዳዮች መሳተፍ እንደሚፈልጉ የገለፁ 34 ከመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ሲሆኑ፥ 10 ከመቶዎቹ በተቃውሞ የፖለቲካ ረድፍ መሰልፍ እንደሚፈልጉ የጥናቱ ውጤት ያመለክታል ማለታቸውንም አካቷል።

በትግራይ ካሉ ወጣቶች መካከል 40 ከመቶዎቹ ትግራይን ለቀው መሰደድ እንደሚሹ የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ጥናት ያሳያል ያለው ዘገባው ሁኔታው በትግራይ ወጣቶች ዘንድ እየታየ ያለ እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጠቁሟል።
ዜና፡ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን መጥለፍ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ወንጀል ጋር በተያያዘ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን እና ደብዳቤዎች ለመጥለፍ ለመርማሪዎች ፈቃድ የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መርማሪ አካል “አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው” የሚመለከተውን የዐቃቤ ሕግ ተቋም የበላይ ኃላፊ በማስፈቀድ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመገናኛ እና የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ ይችላል።

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ በማስመሰል ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ ላይ ይጣል የነበረው ከ5 እስከ 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተሻሽሎ ከ100 እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ሆኗል።

ተጨማሪ ለመመልከት፦ https://wp.me/pfjhHd-1cf
ዜና: #ከዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ከሚላክ ገንዘብ በየዓመቱ በአማካይ ከ4 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር እያገኘሁ ነው ሲል መንግስት ገለጸ

በ2016 በጀት ዓመት 10 ወራት ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ከላከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የሚኒስትሮች ምክር ቤት እያካሄደው በሚገኘው የበጀት አመቱ የመጨረሻዎቹ የ100 ቀናት ግምገማ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት መግለጻቸው ተጠቆመ።

ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ከሚልከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) ባለፉት 5 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ከ4 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው መናገራቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ከዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት የሚላከው የውጭ ምንዛሬ የተሻለና እድገት እያሳየነው ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው መናገራቸውን መረጃው አካቷል።

ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ የሚልኩትን የገንዘብ መጠን ለማሳደግ ገንዘብ የሚልኩባቸውን አማራጮች ቀልጣፋ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስምንት ወራት 1 ሺህ 745 የዳያስፖራ አባላት በሀገር ውስጥ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሂሳብ ቁጥሮችን በመክፈት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ዜና: አዲስ አበባ #ዩኒቨርሲቲ ለ12 ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ12 ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱን አስታወቀ።

ምሁራኑ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸው በማስተማር ውጤታማነት፣ ባሳተሟቸው ጥናታዊ ጹሁፎች፣ ለማህበረሰብ ላበረከቱት አካዳሚያዊ አገልግሎትና በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው የተቋም አስተዳደር ድምር ውጤት መሆኑን ገልጿል።

ወደ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካደጉት መካከል ሁለት ሴት ምሁራን እንደሚገኙበት ያስታወቀው እነዚህም ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር እንጉዳይ አደመ በካሪኩለም ጥናት፣ ፕሮፌሰር ይምጡበዝናሽ ወ/አማኑኤል ደግሞ በሜዲካል ማይክሮ ባዮሎጂ መሆኑን ጠቁሟል።

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት የቀረቡለትን የማዕረግ እድገት ያጸደቀው የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ''ስለ ራስገዝ ዩኒቨርሰቲ ለመደንገግ በወጣ'' አዋጅ ቁጥር 1294/2015 በተሰጠው ስልጣን መሠረት መሆኑን አመላክቷል።

የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸው 12 ምሁራንም፡-

ፕሮፌሰር ይምጡበዝናሽ ወ/አማኑኤል በ ሜዲካል ማይክሮ ባዮሎጂ
ፕሮፌሰር እንጉዳይ አደመ በካሪኩለም ጥናት
ፕሮፌሰር አንተነህ በለጠ በፍርማሴዩቲክስ
ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ በፕላንት ጄኔቲክስ
ፕሮፌሰር አህመደ ሁሴን በ አናሊቲካል ኬሚስትሪ
ፕሮፌሰር ታደሰ እጓለ በማይክሮባዮሎጂ
ፕሮፌሰር ተክለሀይማኖት ኃ/ሥላሴ በፕላንት ባዮቴክኖሎጂ
ፕሮፌሰር ተሸመ ሰንበታ በኮንደንስድ ማተር ፊዝክስ
ፕሮፈፌሰር ሀብቴ ተኪኤ በሜዲካል ኢንቶሞሎጂ
ፕሮፌሰር ቃላብ ባዬ በ ሂዩማን ኒውትሪሽን
ፕሮፌሰር ሰለሞን ሙሉጌታ በአርባን ፕላኒንግ
ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ፍሰሀ በፖሊዮኢንቨሮመንታል ጥናት ናቸው።
በተለያዩ አካባቢዎች 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን መገንባት የሚያስችል የ250 ሚሊየን ዶላር ሥምምነት ተፈረመ

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን ለመገንባት የጤና ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲና #ሩስያ ፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።

ማዕከላቱን ለመገንባት ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ እንደሚፈጁና ወጪውም በሩስያ ፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት የሚሸፈን መሆኑ ተጠቁሟል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በዚህ ጊዜ፤ በሥምምነቱ መሠረት ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት እንደሚቆይና 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን ለመገንባት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ማዕከላቱ በዋናነት በእናቶችና ሕጻናት ጤና፣ በአረጋውያን፣ በወጣቶች እንዲሁም በወሊድ፣ በክትባት፣ በቤተሰበ እቅድና በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ኢዜአ ዘግቧል።

የሩስያ የፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት ግብረ-ሰናይ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኦክሳና ማዮሮቫ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የዜጎችን ጤናማ ሕይወት ለማስጠበቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

==============
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ዩቲዩብ፡ https://rb.gy/bjcbg
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡https://rb.gy/3bghek
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ የሥነ ስርዓትና ፍሬ ነገር ህጎች እየተዘጋጁ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ለመተግበር በአዋጁ የተጠቀሱ ተቋማትን ማቋቋም የሚያስችሉ የሥነ ስርዓትና ፍሬ ነገር ህጎች እየተዘጋጁ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት ጠ/ሚ አብይ አህመድ( ዶ/ር) በተገኙበት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበጀት ዓመቱ የመጨረሻዎቹ 100 ቀናት የህግና ፍትህ ሥርዓቱ ያለበት አፈፃፀም ግምገማ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡

ቀደም ሲል የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን መተግበር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተጠናቅቆ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ፍኖተ-ካርታው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአባልነት የሚሳተፉበት ጊዜያዊ እና ዘላቂ ተቋማዊ የቅንጅት አመራር ሥርዓት ስለሚቋቋምበት ሁኔታ፤ ስለ ሽግግር ፍትሕ ስልቶች አተገባበር ቅደም-ተከተል መካተቱም ተመላክቷል።

የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) የሽግግር ፍትህ ፖሊሲውን መተግበር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መውጣቱን ገልጸው በፖሊሲው የተመላከቱ ተቋማትን ማቋቋም የሚያስችሉ የሥነ ስርዓትና ፍሬ ነገር ህጎች እየተዘጋጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፍትህ ዘርፉን ለማሻሻል በፌደራልና በክልል ደረጃ ገቢራዊ የሚደረጉ ሀገር አቀፍ ህጎችና አሰራሮች መውጣታቸውን ጠቅሰው፣ የአስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅን ማስተግበር፣ የወንጀል ሥነ ስርዓት አጽድቆ ገቢራዊ ማድረግም በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
#አማራ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸው ተገለፀ

በአማራ ክልል ባለፉት 11 ወራት ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት አስታወቀ።

የክልሉ ጤና ቢሮና የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ኃላፊዎችም በበኩላቸው በክልሉ የወባ በሽታ በከፋ ሁኔታ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልፀዋል።

የክልሉ የጤና ተቋማት ኃላፊዎች እንደገለፁት በክልሉ ያለው ግጭት ሳቢያ በተደጋጋሚ የመንገዶች መዘጋጋት የወባ ሥራ ቁጥጥርን አዳክሞታል። የመድኃኒት ስርጭትን ደግሞ አስተጓጉሎታል። ይህም ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል። ህብረተሰቡ ወባን ለመከላከል ያለው ዝቅተናኛ ግንዛቤና ቸልተኝነት ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው ሲሉ ሀላፊዎቹ ገልፀዋል።

የባህርዳር ነዋሪዎችም በበኩላቸው በከተማው የወባ ስርጭት መበራከቱን ይገልጻሉ። የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለም አሰፋ ባለፈው ሳምንት 7ሺህ ሰዎች የወባ ምርመራ አድርገው በ2ሺህ 460 ሰዎች ላይ በሽታው ተገኝቷል ብለዋል፡፡

(ዶቼ ቬሌ)
ዜና፡ #ለፓርላማ የቀረበው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን መጥለፍ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ተቃዋሚዎችን ማሳደጃ እንዳይሆን የምክር ቤቱ አባላት አሳሰቡ

ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች እና አስተያያቶች ካነሱት መካከል በቅርቡ ለእስር ተዳርገው የተፈቱት የፓርላማው አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ይገኙበታል።

ዶ/ር ደሳለኝ ስጋት እና አስተያየት በሚል ባቀረቡት ሀሳብ ለምክር ቤቱ የሚቀርቡ ወንጀል እና ሽብር ነክ አዋጆች አስፈላጊነታቸው እንደተጠበቀ ሁኖ ተቃዋሚዎችን እና መንግስትን የሚተቹ ተቋማት የነዚህ አይነት ህጎች ሰለባ ሁነው ብዙ ጉዳት እንደደረሰባቸው በማውሳት ጥንቃቄ እንዲደረግባቸው አሳስበዋል።

አዋጆቹን ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን ለማሳደድ እንዳያውለው ምን ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ማብራሪያ እንዲሰጥበት በመጠየቅ አዋጆቹ የወንጀል ፍሬ የሆኑትን ብቻ ለይቶ ለመከታተል እና ተቃዋሚዎችን ማሳደጃ እንዳይሆን ተገቢ ድንጋጌዎች እንዲካተቱባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

ሌላ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው በአካል በአዋጁ አንቀጽ “በቂ ቁጥጥር ከማያደርጉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የንግድ ግንኙነት ከመሰረተ ወይንም የነበረውን የንግድ ግንኙነት ካስቀጠለ” የሚለው ሃሳብ አሻሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሃሳቡ ውስብስብ ከመሆኑ ባለፈ ባንኮቹ ትክክለኛ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው መሆናቸውንም ሆነ አለመሆናቸውን ማን ነው የሚያረጋግጠው ሲሉ ጠይቀዋል፤ ውጭ ሀገር ያለን ባንክ እንዴት ነው ማረጋገጥ የምንችለው፣ እነዴት በዝርዝር ማስቀመጥ ይችላል ብለዋል።
https://wp.me/pfjhHd-1cj
ዜና: #የኳታሩ አሚር ከጠ/ሚ አብይ እና #ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሸክ ሀሰን ጋር በተናጠል በስልክ መወያየታቸው ተገለጸ

የኳታሩ አሚር ሸክ ታሚም ቢን ሃመድ አል ታኒ ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር #አብይ አህመድ ጋር በስልክ ማውራታቸው ተገለጸ።

የኳታሩ አሚር ከጠ/ሚኒስትር አብይ ጋር በስልክ ማውራታቸው ከተገለጸ በሰአታት ልዩነት ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሸክ ሀሰን ጋር ማውራታቸውን የኳታር መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

የኳታሩ መሪ ሸክ ታሚም ቢን ሃመድ አል ታኒ ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ጋር የሀገራቱን ግንኙነት መደገፍ እና ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች እንዲሁም አሳሳቢ በሆኑ ቀጠናዊ እና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መክረዋል ብለዋል።

የኳታሩ መሪ ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውጥረት ዙሪያ ስለመወያየታቸው ያሉት ነገር የለም።

የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሸክ ታሚም ቢን ሃመድ አል ታኒ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሸክ ሀሰን ጋር በስልክ መወያየታቸውን ባሳወቁበት ዘገባቸው ሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያዩ ከማለት በቀር ያቀረቡት መረጃ የለም።

መሪዎቹ በሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በቀጠናዊ እና አለምአቀፍ ጉዳዮች ተወያይተዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ከቀናት በፊት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ወደ ኳታር በማቅናት ከሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ጋር መወያየታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል።

አህመድ ሽዴ ከኳታር አቻቸው አሊ ቢን አህመድ አል ኩዋሪ ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያና በኳታር በፋይናንስ፣ በልማት ትብብር እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ መምከራቸውንም አስታውቀዋል።
ዜና፡ ከ #አዋሽ_አርባ ወደ #አዲስ_አበባ የተዘዋወሩት ፖለቲከኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ፤ ሶስት ጋዜጠኞች “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ አቀረቡ

ህዳር 30 ተጠርቶ ከነበረው ሰልፍ ጋር ተያይዞ ከሁለት ወራት በላይ አዋሽ አርባ የወታደራዊ ካምፕ እስር ላይ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ከተዘዋወሩት ተጠርጣሪዎች መካከል ዘጠኙ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ” በእስር ላይ የሚገኙ ሶስት ጋዜጠኞች “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ አቀረቡ።

“ጦርነት ይብቃ፣ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ቃል ህዳር 30 ሰላማዊ ሰልፍ የጠሩት ፖለቲካኞች የተጠረጠሩት “በሁከት እና በብጥብጥ በተለያዩ ነገሮች ላይ በመሳተፍ ህገ መንግስታዊ ስረዓቱን ለመናድ ሲሰሩ” መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

ይህ በእንዲ እያለ የተፈጻሚነት የጊዜ ወሰኑ ባለፈው ሳምንት ካበቃው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ሶስት ጋዜጠኞች፤ “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ለፍርድ ቤት አቅርበዋል። አቤቱታውን በጠበቆቻቸው በኩል ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ጋዜጠኞች #በቃሉ_አላምረው#በላይ_ማናዬ እና #ቴዎድሮስ_ዘርፉ ናቸው።

ሙሉ ዘገባውን ለማግኘት፦ https://wp.me/pfjhHd-1cn
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
በአገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች የማክሮኢኮኖሚ ጉዳት አስከትለዋል _ የአማራ በሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዪ ደሳለኝ ጫኔ ( ዶ/ር)

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው በ31ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ ገንዘብ ሚኒስቴር ያቀረበውን የ2017 የፌዴራል መንግስት የካፒታል እና የመደበኛ ረቂቅ በጀት መግለጫ ከትላንት በስቲያ አድምጧል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተፅዕኖን በተመለከተ ስጋታቸውን አንስተዋል።

የአማራ በሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዪ ደሳለኝ ጫኔ ( ዶ/ር) በ #ኦሮሚያ ለስድስት ዓመታት የዘለቀው ግጥት እና በ #አማራ፣ በ #ትግራይ እንዲሁም በ #አፋር ከሶስት ዓመታት በላይ የተካሄዱ ግጭቶች የማክሮኢኮኖሚ ጉዳት አስከትሏል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ በኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አማራና አፋር በግጭቶች የተጎዱ አካባቢዎች መኖራቸውን አምኗል። ይሁን እንጂ የኢኮኖሚ ማሻሻያው "ጠንካራ እድገት" በማምጣቱን ገልጸዋል።

ይመልከቱ!
ዜና: #ኢትዮጵያ ምንም አይነት “የአቪዬሽን ደህንነት ስጋት የሌለባት ሀገር” ናት ሲል የዓለም አቀፉ አቪዬሽን ድርጅት ኦዲተሮች ማረጋገጫ ሰጥቷል ተባለ

የዓለም አቀፉ አቪዬሽን ድርጅት ኦዲተሮች ባለፉት 10 ቀናት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ደህንነት መፈተሻቸውን የገለጹት በብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት መምሪያ ዳይሬክተር አስራት ቀጀላ ፍተሻው የተከናወነው ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 6 መሆኑን አስታውቀዋል።

በቦሌ ኤርፖርት እና በሌሎች አየር ማረፊያዎች በተደረገው ኦዲት ኢትዮጵያ ምንም አይነት የአቪዬሽን ደህንነት ስጋት የሌለባት መሆኑን የድርጅቱ ገምጋሚዎች መገልፃቸውን ዳይሬክተሩ የፍተሻውን መጠናቀቅ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ አመላክተዋል።

እንዲስተካከሉ አስተያየት የተሰጠባቸውን የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እና ሌሎች ጉዳዮች በፍጥነት እንደሚስተካከሉም ጠቁመዋል።

ከሲቪል አቪዬሽን ደህንነት አንፃር በድርጅቱ መስፈርት መሰረት በቁጥር የተሟላ የኦዲቱ ሪፖርት በቅርቡ አዘጋጅተው እንደሚያስረክቡ ተጠቅሷል።

ይህ የኦዲት ውጤት በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ወደ ስራ እንዲገቡ፣ ለሀገሪቱ የቱሪዝም እና የአቪዬሽን ዘርፍ እድገት አስተዋፅኦው የላቀ ነው ተብሏል።

ለዚህ ውጤት መገኘት በዘርፉ በቅንጅት የሚሰሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት፣ ፌደራል ፖሊስ ፣ ጉሙሩክን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና ትልቅ እንደነበርም በመግለጫው ተጠቅሷል።
ዜና: በበጀት ዓመቱ የመዲናዋን ሰላምና #ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ የከተማዋ ከ140 ሺህ በላይ የሰላም ሠራዊት የነቃ ተሳትፎ ነበረው ተባለ

በመዲናዋ ሰላምና ጸጥታን አስተማማኝ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ የተቀናጁ አሠራሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ #የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።

ሃላፊዋ የመዲናዋን ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝ መልኩ በማስጠበቅና ሕገ-ወጥነትን በመከላከል ቅንጅታዊ አሠራሮች ተግባራዊ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።

በዚህ ረገድ ከ21 የተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሠራቱን አስታውሰው፤ ይኸው ውጤታማ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር በወንጀል መከላከል፣ የፀረ-ሰላምና ጽንፈኛ ኃይሎችን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ ረገድ በርካታ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ተብሏል።

በወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግም እንዲሁ።

የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ ጌታሁን አበራ፤ የወንጀል መከላከሉ ሥራ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የላቀ አስተዋጽዖ ማበርከቱን አንስተዋል።

ከ140 ሺህ በላይ የሰላም ሠራዊት በየአካባቢያቸው የሰላምና ጸጥታ ሥራ በመሥራት የነበራቸውን የነቃ ተሳትፎም ለአብነት መጠቀሱን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ዩቲዩብ፡ https://rb.gy/bjcbg
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡https://rb.gy/3bghek
ዜና: #በጂቡቲ የሚገኝ የሶስት መርከቦች የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ለማጓጓዝ ጥረት እየተደረገ ነው ተባለ

ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን እና ይህም የመንግስት አፈጻጸም 69 በመቶ መሆኑን የሚያመላክት መሆኑ ተገለጸ።

በጂቡቲ የሚገኝ የሶስት መርከቦች የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ለማጓጓዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ በጂቡቲ ከሚገኘው የአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴ ጋር በኤምባሲው ቅጥር ግቢ በመገኘት በአፈር ማዳበሪያ ዝውውር አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት ማካሄዳቸው ተገልጿል።

የማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት እስከአሁን 27 የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች ጂቡቲ የደረሱ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የ24 መርከቦች የአፈር ማዳበሪያ ጭነት ከጂቡቲ ወደብ ወደ #ኢትዮጵያ እየተጓጓዙ መሆኑን በመግለጽ፣ ቀሪ 3 መርከቦች በኦፕሬሽን ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

በዘህ መሰረት እስከአሁን 1,334,487.1 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በተሳካ ሁኔታ ወደ ሀገር ውስጥ ማጓጓዝ በመቻሉ ከዓመታዊ እቅድ 68.78% መሳካቱን ኮሚቴው መግለጹን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ሚኒስትሩም እስከአሁን በተሰሩ የማጓጓዝ ስራዎች ኮሚቴውን በማመስገን፣ አሁንም የአፈር ማዳበሪያ ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ኮሚቴው በማጓጓዝ ሂደቱ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች ተቀርፈው ቀሪ የማዳበሪያ ጭነቶች በተጠናከረ መልኩ ተቀናጅቶ በመስራት በሰዓቱ ለአገራችን ገበሬዎች ማድረስ እንዲቻል አቅጣጫ መስጠታቸው ተጠቁሟል።
#ኦጋዴን ከ21 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩ ተረጋገጠ_ የማዕድን ሚኒስቴር

#ሶማሌ ክልል ኦጋዴን 19 ጉድጓዶችን በመቆፈር በተደረገ ዳሰሳ "21 ቢሊዮን 336 ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ እንዳለ" መረጋገጡን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማትዮስ፤ በሌሎች ስድስት ቦታዎች ላይም ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት መኖሩን ኢፕድ ተናግረዋል፡፡

#ኦጋዴን#መቀሌ#መተማ#ደቡብ_ኦሞ እንዲሁም #ጋምቤላ አካባቢዎች በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡

እንደ አቶ ሚሊዮን ገለጻ፤ በክልሉ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ በቅርብ ዓመታት ወደ ምርት ለማስገባት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ሌሎች በፍለጋ ምዕራፍ ላይ ያሉትም በአጭር ጊዜ ውጤታማ የሚሆኑበት አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ዩቲዩብ፡ https://rb.gy/bjcbg
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡ https://rb.gy/3bghek
ዜና: #የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ ሀብቱ 672 ቢሊየን ብር ቢደርስም 367 ቢሊየን ብሩ በዕዳ የተመዘገበ ነው ተባለ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቅርቡ በሚያካሂደው የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ማሻሻያ ዙሪያ ከተቋማት እና ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር እየመከረ መሆኑን አስታውቋል።

የታቀደው የታሪፍ ክለሳ የኢነርጂ ዘርፉን ለማሳደግ እና አገልግሎቱን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ ሀብቱ 672 ቢሊየን ብር ቢደርስም 367 ቢሊየን ብሩ በዕዳ የተመዘገበ ነው ሲሉ የተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ ከሚዲያ ሃላፊዎች ጋር ባካሄዱት ምክክር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከውሃ 4 ሺህ 820 ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 404 ሜጋ ዋት እና ከእንፋሎት 32 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጨች ትገኛለች ብለዋል።
https://wp.me/pfjhHd-1cq
ዜና: በአሁኑ ወቀት “80 ወይም 90 በመቶ የሚሆነው #የአማራ አካባቢ በፋኖ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ይገኛል” - እስክንድር ነጋ

የፋኖ ታጣቂ ቡድን መሪ ከሆኑት አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞው ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ እስክንድር ነጋ ከመንግሥት ጋር ድርድር ለማድረግ ገና ከውሳኔ አልተደረሰም ሲሉ አስታወቁ።

እስክንድር ነጋ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በንግግር ለመፍታት ከመንግሥት ጋር ሊደረግ ስለሚቻልበት ውይይትን በተመለከተ “ገና ከውሳኔ አልደረስንም” ብለዋል።

“ከመንግሥት ጋር እየተዋጉ ያሉ በርካታ የፋኖ ቡድኖች አሉ። እያንዳንዱ ቡድን እራሱን የቻለ ነው” ያሉት እስክንድር፤ በክልሉ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የተለያዩ የፋኖ ቡድኖችን ለማዋሃድ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

“በአሁኑ ወቅት አንድነት ለመፍጠር እየተነጋገርን ነው። ይህ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ከመንግሥት ጋር ሊደረግ ስለሚችል ድርድር ውሳኔ ላይ መድረስ ይቻላል።”

እስክንድር ነጋ “በመርህ ደረጃ ድርድር ተቀባይነት ያለው ነገር ነው” ካሉ በኋላ፣ በአፍሪካ ያለውን ተሞክሮ በማንሳት ከብዙ የሰው እልቂት እና የንብረት ውድመት በኋላ ተዋጊ ኃይሎች ወደ ድርድር ሲመለሱ ተመልክተናል ብለዋል።

በአሁኑ ወቀት “80 ወይም 90 በመቶ የሚሆነው የአማራ አካባቢ በፋኖ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ይገኛል” ያሉት እስክንድር፤ የመንግሥት ኃይሎች ዋነኛ ጥረት ሆኖ የቆየው በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችን ተቆጣጥሮ ማስተዳደር ነው ይላሉ።

በአማራ ክልል ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ መኖሩን ያስታወሱት እስክንድር፤ የፋኖ ኃይሎች ተቆጣጥረው በሚገኙባቸው አካባቢዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች የሰብዓዊ እርዳታ ሥራ እንዲሰሩ ፍቃደኞች ነን ማለታቸውን ከቢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዜና: በሀገሪቱ በ2023 ከተመዘገቡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በመንግስት #የጸጥታ ሀይሎች የተፈጸሙ ናቸው - የመንግስታቱ ድርጅት

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽን #በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታን አስመልክቶ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በኢትዮጵያ በተለይም #በኦሮምያ እና #አማራ ክልሎች የሚፈጸሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ ናቸው ብሏል።

በዘፈቀደ የዜጎችን መብት መግፈፍ፣ በፖለቲካ ምክንያት የሚደርስ የአካል ማጉደል፣ የወሲብ ጥቃት፣ የመሰብሰብ ነጻነትን መግፈፍ፣ የዘፈቀደ እስር፣ የመናገር ነጻነት መግፈፍ እገታ እና መሰወር የመሳሰሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ በ2023 መመዝገባቸውን አስታውቋል።

በሀገሪቱ በተደጋጋሚ ከተጣሱ ሰብአዊ መብቶች መካከል ዋናዋናዎቹ የዘፈቀደ እስር እና የንጹሃን ግድያዎች መሆናቸውን ጠቁሟል።

የጥቃቱን 70 በመቶ ፈጻሚዎች የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ማለትም የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የፌደራል እና ክልል ፖሊስ አባላት እና በመንግስት የሚደገፉ የሚሊሻ ታጣቂዎች ናቸው ብሏል።
https://addisstandard.com/Amharic/%e1%89%a0%e1%88%80%e1%8c%88%e1%88%aa%e1%89%b1-%e1%89%a02023-%e1%8a%a8%e1%89%b0%e1%88%98%e1%8b%98%e1%8c%88%e1%89%a1-%e1%8b%a8%e1%88%b0%e1%89%a5%e1%8a%a0%e1%8b%8a-%e1%88%98%e1%89%a5%e1%89%b5-%e1%8c%a5/
ዜና: የሚንስትሮች ምክር ቤት የንብረት ታክስ ረቂቅ #አዋጅን በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ተገለጸ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትላንት ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ተወያይቶ ውሳኔ ካዳለፈባቸው ጉዳዮች መካከል የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ይገኝታል። ከጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ እንዳስታወቀው አዋጁ ሁለት ግቦችን ለማሳካት በሚል እንዲጸድቅ ተፈልጓል፤ በከተሞች ነዋሪ በሆነው ሕዝብ መካከል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማስፈን፣ የመንግስትን ገቢ በማሳደግ የመሰረተ ልማት ማሻሻያዎችን በቀጣይነት ለመተግበር።

አዋጁ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ያመላከተው ምክር ቤቱ ክልሎችም ይህንን አዋጅ መሰረት በማድረግ ከተጨባጭ ሁኔታቸው ጋር በተጣጣመ አኳኋን የየራሳቸውን የንብረት ታክስ ህግ እንዲያወጡ ያስችላል ብሏል።

በዚሁ መሰረት ይህንን ለማስፈጸም የሚረዳ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ መቅረቡን ጠቁሟል።

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ዩቲዩብ፡ https://rb.gy/bjcbg
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡https://rb.gy/3bghek