Addis Standard Amharic – Telegram
Addis Standard Amharic
18K subscribers
4.75K photos
123 videos
3 files
3.78K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
ዜና፡ የፈንታሌ ሚዲያ መስራች ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉ "ማንነታቸው ካልታወቁ ሰዎች" ለማምለጥ ሲሞክር ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ገለፀ

የፈንታሌ ሚዲያ መስራች ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉ “ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች” በአዲስ አበባ ከተማ “ሊፈፀምብኝ ነበር” ካለው ጥቃት ለማምለጥ ሲሞክር ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፀ።

ጋዜጠኛ ፋኑኤል በደረሰበት ጉዳት ሳቢያም ለመራመድ ከሶስት እስከ ስድስት ወር ሊፈጅበት እንደሚችል በህክምና ባለሞያተኞች እንደተገለጸለት ተናግሯል። ጋዜጠኛው ስለደረሰበት ጉዳት ለአዲስ ስታንዳርድ ሲያብራራ፣ ከወር በፊት ማለትም ህዳር 10/2018 ዓ.ም ስምንት ሰዓት አከባቢ “ሲቪል የለበሱ ሰዎች እንደሚፈልጉኝ” ከቤተሰብ ሰማሁ ሲል ይጀምራል።

በወቅቱ “የቅርብ ጓደኛው ጋር በመሄድ ጉዳዩን እንደነገረው እና ገስት ሀውስ ብታርፍ ይሻላል ብሎኝ ወደዚያው በማቅናትት እዛው ክፍል አግኝቼ ገባው” ሲል ጋዜጠኛው ገልጿል።

ሆኖም የቅርብ ጓደኛው ከሄደ ከ50 ደቂቃ በኋላ ያረፈበት ክፍል በሩ በጣም ይደበደብ እንደጀመረ ጠቅሶ፣ በወቅቱ “ክፈት የሚል እና ሀይለቃል የተሞላበት ቃል እሰማ ነበር” ብሏል።

“በሩን በጣም እየገፉት ሲመጡ ክፍሏ ከጎን የበረንዳ ኮሪደር ያላት በመሆኑ ኮሪደሩ ጋር ሆኜ ተዘጋጀሁ” ያለው ጋዜጠኛው፣ “በወቅቱ ደብድበው ሞቶ ተገኘ ልባል እችላለሁ የሚል ስጋት አደረብኝ በዚህም አራት ሜትር አከባቢ ከሚረዝም ሁለተኛ ፎቅ ላይ ዘለልኩ” ሲሉ ተናግሯል።

አክሎም “ዘልዬ ከወደኩኝ በኋላ ልነሳ ስል ራሴን ሳትኩ ጭልም አለብኝ” ሲሉ ገልጾ፣ “ቀና ስል አጥንቴ ተሰብሯል። በአከባቢዬ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ነበሩ። "ይሄን እድል ደግመህ አታገኝም" ብለውኝ ሄዱ ከዛም ሰዎች ወደ ሆስፒታል ወሰዱኝ ብሏል።

“ከዛ በኋላ ለ20 ምናምን ቀናት ለማንም ጉዳዩን አልተናገርኩም ነበር” ያለው ጋዜጠኛ ፋኑኤል፣ ነገር ግን ጉዳዩ “ከሚዲያ ስራው ጋር የተገናኘ ነው” ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል።

ተጨማሪ ያንብቡ፡ https://addisstandard.com/Amharic/?p=10205
#አዲስ_አበባ ከተማ በአጥር የተዘጉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በግብረ ኃይል የማስከፈት ስራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ በከተማ ተለያዩ አካባቢዎች በአጥር የተዘጉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በግብረ ኃይል የማስከፈት ስራ በትናንትናው ዕለት መጀመሩን የከተማዋ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ይህን እርምጃ መውሰድ የጀመረው፣ ከሳምንታት በፊት በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን አጥረው የዘጉ ግለሰቦች መንገዶቹን ከታኅሣሥ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ሰባት ተከታታይ ቀናት ውስጥ ክፍት እንዲያደርጉ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ባለመሆኑ ነው።

ባለስልጣኑ ትናንት ባጋራው መረጃ፣ የደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ኔትዎርክ ማኔጅመንት ቡድን መሪ ኢንጅነር ቢሊሱማ በዬቻ፤ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በግለሰቦች በአጥር መዝጋታቸው፤ የህብረተሰቡን በመንገድ መሰረተ ልማት የመጠቀም መብት የሚጋፋና ለትራፊክ ፍሰት መስተጓጎል መንስኤ እየሆነ እንደሚገኝ ገልፀዋል ብሏል፡፡

በመሆኑም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቃሊቲ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ፤ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በአጥር የዘጉ አካላት፣ አጥሩን እንዲያነሱ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ቢሆንም፤ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ባለመነሳቱ ከወረዳው የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በግብር ኃይል እንዲነሳ መደረጉን ገልጸዋል።

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid0K763TCGodEANKMS2Ca5DFSMcWnBgU7U3uPXE2hQX8GfvsjPhUJKzGG8uwEp68VxDl
ዜና: ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የጤና ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ፤ የአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግም ቃል ገብተዋል

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ በጋራ 1.466 ቢሊዮን ዶላር ለመመደብ የሚያስችል የአምስት ዓመት የጤና ትብብር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ እስከ 1.016 ቢሊዮን ዶላር የምትመድብ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ከአገር ውስጥ ሀብት 450 ሚሊዮን ዶላር እንደምትሸፍን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ ከጎርጎሮሳውያኑ 2026 እስከ 2030 ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ይሆናል ተብሏል።

የአሜሪካ መንግሥት በተጨማሪም በሥራ አፈፃፀም ላይ የተመሠረተ 150 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስቴር አመልክቷል። ድጋፉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከሆነ የአሜሪካ አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ ወደ 1.166 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል የተባለ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያ ከምትሸፍነው ጋር ተደምሮ የአምስት ዓመቱን የጤና ትብብር ጥቅል ማዕቀፍ 1.616 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ስምምነቱ “አሜሪካ ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ የሚያረጋግጥ ነው” ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ የጤና ኢንቨስትመንቷን ለማስፋፋት የወሰደችውን ውሳኔም አድንቀዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የመግባቢያ ስምምነቱን በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለውን መተማመን የሚያሳይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

ተጨማሪ ይመልከቱ:
https://addisstandard.com/Amharic/?p=10213&amp=1
ዜና፡ በ #ጋምቤላ ክልል ስደተኞችን ኢላማ ያደረገ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ውጥረቱን ሊያባብስ እንደሚችል የስደተኞች ኮሚሽን አስጠነቀቀ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ስደተኞችን ኢላማ በማድረግ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጨ ያለው ሀሰተኛ መረጃ አሳሳቢ መሆኑን ገልጾ፣ ሁኔታው በአስቸኳይ እልባት ካልተሰጠው ውጥረቱን ሊያባብስ እንደሚችል አስጠነቀቀ።

ኤጀንሲዉ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ የአሳሳች ትርክት ስርጭት በስደተኞች እና በአስተናጋጅ ማኅበረሰቦች ላይ አደጋ እንደሚፈጥር በመጠቆም፣ ለሁኔታው ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ጥሪ አቅርቧል።

አክሎም እንዲህ ዓይነት ንግግሮች በንጹሐን ዜጎች ላይ አደጋ እንደሚፈጥሩና አብሮ የመኖር እሴትን እንደሚጎዱ የገለጸው መግለጫው፣ ሁሉም አካላት ከጥላቻ ንግግር እንዲታቀቡ አሳስቧል።

የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽኑ በሁኔታው መባባስ የምግብ እና የውሃ አቅርቦትን ጨምሮ አንዳንድ ሰብአዊ አገልግሎቶችን ለጊዜው ለማቋረጥ መገደዱን ገልጿል። ስደተኞች ከሀገራቸው ጥቃት ሸሽተው ደህንነት ፍለጋ የመጡ በመሆናቸው፣ በጅምላ ተጠያቂነት ሊፈረጁ አይገባም ሲልም አሳስቧል። ኤጀንሲው የሲቪል እና ሰብአዊ ባህሪ ያለው ጥገኝነት “ለድርድር የማይቀርብ መርህ” መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።

ዝርዝሩን ለማንበብ፡ https://addisstandard.com/Amharic/?p=10216
ዜና: ምርጫ ቦርድ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዜጎች የመደራጀት እና የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት መብት ላይ የሚፈፀሙ ጥሰቶች እንዲቆሙ አሳሰበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዜጎች የመደራጀት እና የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ የሚፈፀሙ ጥሰቶች እንዲቆሙ አሳሰበ።

ቦርዱ ዛሬ ታህሳስ 15/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የኮንቶማ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” መሥራቾች ፓርቲ ለመመሥረት የሚያስፈልጉ ሁሉንም ሕጋዊ ሠነዶች አሟልተው የመሥራች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡታጅራ ከተማ እንደሚያደርጉ ለቦርዱ ማሳወቃቸውን ገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎ ቦርዱ ለክልሉ መንግሥት አስተዳደር፣ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለምሥራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ ለቡታጅራ ከተማ አስተዳደር፣ ለማረቆ ልዩ ወረዳ ኮማንድ ፖስት እና ለቡታጅራ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ለመሥራቾቹ የፀጥታ ድጋፍ ትብብር እንዲደረግላቸው በደብዳቤ ማሳወቁን ገልፆ የቦርዱ ባለሙያዎችም በሕጉ መሠረት በቦታው በመገኘት ታዝበው ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተመድበው እንደነበር አስታውሷል።

ሆኖም የክልሉ የፀጥታ አካላት፤ ጉባዔ መደረግ የማይችልበትን ሁኔታ በጽሑፍ ለቦርዱ ሳያሳውቁ መሣሪያ የታጠቁ የቡታጅራ ከተማ የፀጥታ አካላት በጉባዔው ዕለት “ከተማው በኮማንድ ፖስት ሥር ስለሆነች መሰብሰብ አይቻልም” በሚል ለስብሰባ የመጡ የፓርቲው መሥራች አባላቶችን ከአዳራሽ በማስወጣት በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው ቦርዱ በታዛቢነት ከላካቸው ባለሞያዎቹ ሪፖርት መረዳት እንደቻለ መግለጫው አመልክቷል፡፡

ተጨማሪ ይመልከቱ:
https://addisstandard.com/Amharic/?p=10219
#ኢትዮጵያ_ንግድ_ባንክና#ኢትዮጵያ_አየር_መንገድ የ27.8 ቢሊዮን ብር ብድር ተፈራረሙ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሠራተኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል የ27.8 ቢሊዮን ብር ብድር ለማቅረብ የሚያስችል "ታሪካዊ" የተባለ ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪውቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ትላንት ታኅሣሥ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርመዋል።

አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ባንኩ የኅብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የብድር አገልግሎቱን እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በሁለቱ ግዙፍ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተቋማት መካከል የተደረገው ይህ ስምምነት በዓይነቱ ልዩና ታሪካዊ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለዉም ለዚህ ስኬት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ ስምምነቱ የአየር መንገዱን ሠራተኞች የቤት ችግር ለመፍታት ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለዉም ብድሩ ለአምስት ሺህ የአየር መንገድ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ወጪን ለመሸፈን የሚዉል መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ መስፍን ፣ አየር መንገዱ የሠራተኞቹን ችግር ለመቅረፍ ባንኩን በአጋርነት መምረጡንና ለተደረገው ትብብር በማኔጅመንቱና በሠራተኛ ማኅበሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለ #ሕፃፅ ተፈናቃዮች የሰብአዊ ድጋፍ አንዳልደረሳቸው የሚገልፁ መረጃዎችን “የተሳሳቱ” ናቸው ሲል አስተባበለ

#ኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በ #ትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ በሚገኘው ሕፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ ድጋፍ አንዳልደረሳቸው የሚገልፁ መረጃዎችን “የተሳሳቱ ናቸው" ሲል አጣጥሏል።

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የተፈናቃዮች የሰብአዊ ድጋፍን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሕፃፅ የሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እንዳልደረሳቸው የሚገልጹ ዘገባዎች “የተሳሳቱ” እና “የመጠለያ ጣቢያውን አጠቃላይ እውነታ የማይወክሉ” ናቸው ብሏል።

መንግሥት በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ዓመቱን ሙሉ የምግብ ድጋፍ ሲያቀርብ መቆየቱን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ከመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁኑ የታኅሣሥ ወር ድረስ “ያልተቆራረጠ እና የተሟላ” ሰብአዊ እርዳታ እየተሰራጨ እንደሚገኝ በመረጃዎቹ ማረጋገጡን አስፍሯል።

በመግለጫው ዝርዝር መረጃ መሠረት፣ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በአስገደ ወረዳ ሕፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ 14 ሺህ 413 ዜጎች ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል። በተጨማሪም ከአጎራባች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን ጨምሮ "በመስከረም ወር 16 ሺህ 775፤ በጥቅምት ወር 18 ሺህ 290፤ በኅዳር ወር 17 ሺህ 813 እንዲሁም በታኅሣሥ ወር የሚያስፈልገው ለ14 ሺህ 413 ዜጎች የሚያስፈልግ ምግብ ተሰራጭቷል" ሲል ኮሚሽኑ በዝርዝር አስቀምጧል።

በዚህም
https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid0SiJBRD3Q5R3C7KbsxJTWYZSjqjsHoD27BEmYPUR5TK6ua8NxyPDYDrmqNY2Esyhel
ዜና፡ ጠ/ሚ ዐቢይ ከዊሊያም ሩቶ ጋር ያደረጉት ውይይት ሳፋሪኮም እና ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ቀንድ በጋራ ለመስራት እንዲችሉ ድጋፍ መስጠቱ ተገለፀ

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መካከል በአዲስ አበባ የተካሄደው ውይይት፤ ሳፋሪኮም እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ እንዲሰሩ የፖለቲካ ድጋፍ አስገኝቷል ተባለ። ይህም በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የዲጂታል እና የመሠረተ ልማት ትብብር ለማሳደግ አዲስ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።

ከውይይቱ በኋላ የወጡ መግለጫዎች፤ መሪዎቹ በሁለቱ የቴሌኮም ኩባንያዎች መካከል ስልታዊ አጋርነት እና ኢንቨስትመንት እንዲኖር ለመደገፍ መስማማታቸውን አመልክተዋል። ስምምነቱ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር እና ቀጣናዊ ግንኙነትን ለማስፋፋት እየተደረገ ያለው ሰፊ ጥረት አካል መሆኑም ተጠቁሟል።

መሪዎቹ የዲጂታል መሠረተ ልማት ለንግድ እና ለፈጠራ እድገት ቁልፍ መሆኑን ገልጸው፤ ለአፍሪካ የልማት፣ የሰላም እና የመረጋጋት ጉዞ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሜ አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መግለጫ፤ ውይይቱ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር እና ለሁለቱም አገራት ዜጎች ተጨባጭ ጥቅም በሚያስገኙ ተግባራት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም “የኢኮኖሚ ትብብርን ለማሳደግ፣ ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈን እና ሕዝቦቻችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ለመደገፍ በጋራ እንሰራለን” ብለዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:
https://addisstandard.com/Amharic/?p=10221&amp=1
ዜና: ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ የፀጥታ ችግር በሚስተዋልባቸዉ የክልሉ አካባቢዎች ሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ የፀጥታ ችግር በሚስተዋልባቸዉ የክልሉ አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ ከምሽት 2 :00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 :00 ሰዓት ድረስ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።

የክልሉ መንግሥት ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ በክልሉ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በተጠቀሰው ጊዜ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ የተሽከርካሪም ሆነ የሰው እንቅስቃሴ የተከለከለ መሆኑን ገልጿል።

መግለጫው ከተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ውጪ የትኛውም ቦታ ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ገልጾ፣ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተጣሉ ክልከላዎችን በማክበርና በማስከበር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስቧል።

ተጨማሪ ይመልከቱ:
https://addisstandard.com/Amharic/?p=10226&amp=1
ዜና: ሳይንሳዊ ያልሆነና #ለጤና ጠንቅ የሆነ የቆዳ መድኃኒት በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያመርት የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

ለቆዳ በሽታ ፈውስነት ይውላል የተባለን ምንጩ ያልታወቀ መድኃኒት በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያመርትና ሲያከፋፍል የነበረ ግለሰብ ከነተባባሪው በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ።

ታኅሣሥ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በተከናወነ ኦፕሬሽን የባለሥልጣኑ ኢንስፔክተሮች ከልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጋር በመተባበር ባደረጉት ክትትል ተጠርጣሪው እጅ ከፍንጅ መያዙ ተገልጿል።

ምርቱን ለደንበኞች በሞተር ሳይክል ሲያደርስ የነበረ ተባባሪውም አብሮ በቁጥጥር ስር መዋል ችሏል።

በኦፕሬሽኑ ወቅት ግለሰቡ ለመድኃኒት ቅመማ መዋል የማይችሉ ስምንት የተለያዩ ኬሚካሎችን እና ሰባት ዓይነት መድኃኒቶችን በመቀላቀል ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የሌለው ውህድን ጨምሮ ምንጫቸው የማይታወቅ በ53 ጠርሙስ የተዘጋጁ ኬሚካሎች መገኘታቸውን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

ተጠርጣሪው “ISRAELOHIM PHARMA MEG AND IMPORT” የሚል የሐሰት የድርጅት ስም በመለጠፍ ኅብረተሰቡን ሲያታልል መቆየቱና ከፌዴራልም ሆነ ከአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ምንም ዓይነት የአምራችነትም ሆነ የቅመማ ፈቃድ የሌለው መሆኑ ተረጋግጧል።

ባለሥልጣኑ እንደገለጸው፣ ግለሰቡ የቆዳ በሽታን የሚያድን ዋና ንጥረ ነገር ሳይኖረው ፣ በዘፈቀደ መድኃኒቶችን እየፈጨ ከኬሚካሎች ጋር በመቀላቀል ለኅብረተሰቡ ጤና ጠንቅ የሆነ ምርት ሲያከፋፍል ነበር ብሏል።

ኅብረተሰቡ የጤና...

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid0RNsGSkaHhpQycPagKG1iQdvvtLpks8y7QiCEA2Qh9QxKytqTt4Vb7ZedK1gAwUhYl
ዜና: በጋምቤላ ክልል በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ቢያንስ 47 ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ፤ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎችን እያከመ እንደሚገኝ አስታወቀ

በጋምቤላ ክልል በተቀሰቀሰ ግጭት በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ቢያንስ 47 ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ፤ ዓለምአቀፉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በዚያው ዕለት ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎችን ማከሙን አስታውቋል።

ትናንት ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ታርፓም ንዑስ ከተማ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 47 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የጤና ባለሙያ እንደተናገሩት ከሆነ፣ “ይህ ቁጥር በመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊያሻቅብ ይችላል”።

“በሰማሁት መረጃ መሠረት 47 ሰዎች ሞተዋል” ያሉት ምንጩ፤ “በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ የተቃጠሉ አንዳንድ ሰለባዎች እስካሁን በሟቾች ቁጥር ውስጥ ሳይካተቱ ሊቀሩ እንደሚችሉ” አክለው ገልጸዋል። አክለውም “ነዋሪዎች አሁንም ሟቾችን እየቀበሩ ነው” ብለዋል።

ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በበኩሉ ትናንት ታህሳስ 15/ 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ በጋምቤላ ክልል ያለው ግጭት ከትናንት ማለዳ ጀምሮ መጠናከሩንና ተቋሙ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎችን መቀበሉን አስታውቋል። ግጭቱ የሚቀጥል ከሆነ በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ ተጎጂዎች ሊመጡ እንደሚችሉም አስጠንቅቋል።

አንድ የአከባቢው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ጥቃቱ መፈፀሙን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል፤ ይሁን እንጂ ባለሥልጣናቱ እስካሁን የተረጋገጠ የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥር እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ጥቃቱ ከድንበር ማዶ በመጡ አካላት የተፈጸመ ነው የሚለውን መረጃ “ክስ” ሲሉ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ወደ ጋምቤላ ከተማ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና ሕክምና ፍለጋ የሚመጡ ሰዎች ጭምር መገደባቸውን አረጋግጠዋል።

ዝርዝር ዘገባውን ይመልከቱ:
https://addisstandard.com/Amharic/?p=10238
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
የኢትዮጵያን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በቅርበት ይከታተሉ

#ኢትዮጵያ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ አዲስ ስታንዳርድ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ያዘጋጀውን የምርጫ መረጃ ገፅ ይፋ ማድረጉን ሲገልፅ ደስታ ይሰማዋል። በገፁ ከዋና ዋና የፖለቲካ ተዋናዮች እስከ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር፣ እንዲሁም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚወጡ ወቅታዊ መረጃዎችን በአንድ ቦታ ያገኙበታል።

በተጨማሪም ከዜና ባሻገር በምርጫው ላይ ግልፅነት የሚያመጡ ልዩ ቃለ-መጠይቆች፣ ጥልቅ ትንታኔዎችን፣ የባለሙያ አስተያየቶችና ጥልቅ ምልከታዎች እንዲያገኙ ያስችልዎታል።

መራጭ፣ ጋዜጠኛ፣ ተመራማሪም ቢሆኑ ወይም ጉዳዩ የሚመለከትዎት ዜጋ፤ ይህ ገፅ ተዓማኒ የምርጫ መረጃ መዳረሻዎ ነው።

🔗 አሁኑኑ ይመልከቱ፦ https://addisstandard.com/amharic-election2026/
“ቤተሰብን ሊያኖር የሚችል ዝቅተኛ የመነሻ ደመወዝ ወለል እንዲወሰን እየተሰራ ነው”_#ኢሠማኮ

“በኢትዮጵያ ቤተሰብን ሊያኖር የሚችል የግል ድርጅት ሠራተኞችን ዝቅተኛ የመነሻ ደመወዝ ወለል ለማስወሰን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን” የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አስታወቀ።

የኮንፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ድሪብሳ ለገሰ፤ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የግል ሠራተኞች የመነሻ ደመወዝ ወለል ሳይወሰን መቆየቱን ገልፀዋል።

አክለውም በአሁኑ ጊዜ ይህንን ችግር ለመፍታትና ቤተሰብን ሊያኖር የሚችል የመነሻ ደመወዝ ወለል የሚወስን ቦርድ ለማቋቋም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የቦርዱን ማቋቋሚያ ደንብ በተመለከተ ኮንፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ግብዓት መስጠቱን የጠቀሱት አቶ ድሪብሳ፤ ቦርዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋቁሞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ የመነሻ ደመወዝ ወለል መወሰኑ የሠራተኞችን ቅሬታ ከመፍታቱም ባለፈ፣ ወቅታዊውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው መናገራቸውን የዘገበው ኢፕድ ነው።

ከዚህ ቀደም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የግል ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው የደመወዝ ጭማሪ እንዲያደርጉ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን እንዲወስን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በተደጋጋሚ መጠየቁ አይዘነጋም።

የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ዩቲዩብ፡ https://rb.gy/bjcbg
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
#እንግሊዝ መንግሥት ለ #ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ደገፈ

#ዩናይትድ_ኪንግደም መንግሥት የማርበርግ የቫይረስ በሽታን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያግዙ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የእንግሊዝ መንግሥት ላደረገው ወቅታዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ሚኒስትሯ ይህ ድጋፍ ድንበር አቋርጠው የሚመጡ በሽታ አምጪ ተህዋሲያንን ለመዋጋትና የጤና ተቋማት ለድንገተኛ አደጋዎች የሚሰጡትን ምላሽ ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የተለገሱት መሣሪያዎች በተለይም በወረርሽኝ መከላከል ግንባር ቀደም ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች ደህንነት መጠበቂያ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ዶ/ር መቅደስ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የዩኬ አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው፣ ዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያ የሕክምና መሣሪያዎችን በማምረት ረገድ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

አምባሳደሩ የሁለቱ ሀገራት ትብብር ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉራዊ እና ለዓለም አቀፍ የጤና ደህንነት ያለውን ፋይዳ ላይ እንደነበር ተገልጿል።

አክለውም "ጠንካራ የጤና ሥርዓቶች ድንበር ተሻጋሪ አደጋዎችን የሚፈጥሩ ወረርሽኞችን ለመከላከል እና ለመቋቋም ወሳኝ ናቸው" ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ይህ ድጋፍ የግል መከላከያ መሣሪያዎችን እና ወሳኝ የምርመራ ኪቶችን ያካተተ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የወረርሽኝ መከላከል ዝግጁነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
#ሳፋሪኮም_ኢትዮጵያ በዳታ ጥቅል አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማረ ማድረጉን አስታወቀ

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የሥራ ማስኬጃ እና የኢንቨስትመንት ወጪን ታሳቢ በማድረግ፣ በሞባይል የዳታ ጥቅል አገልግሎቶቹ ላይ የዋጋ ማስተካከያ ማድረጉን ገለጸ።

ኩባንያው ለደንበኞቹ ባስተላለፈው መልእክት፣ ይህ የዋጋ ማመጣጠን እርምጃ የተወሰደው አስተማማኝ እና ጥራት ያለው የሞባይል ዳታ አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስቀጠል መሆኑን ገልጿል።

ሳፋሪኮም በመልእክቱ "ለ12 ሚሊዮን ደንበኞቻችን ምርጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ ቁርጠኛ ነን" በማለት፣ ደንበኞቹ ላሳዩት እምነት እና ቀጣይነት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል።

ምንም እንኳ ኩባንያው የዋጋ ማስተካከያው የተደረገበትን ዝርዝር የኢኮኖሚ ምክንያቶች ባይዘረዝርም፣ በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት እና የውጭ ምንዛሬ ለውጥ በቴሌኮም ዘርፉ ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም  ከሚያዝያ 2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም በነበረው ግማሽ በጀት ዓመት፣ የነበረበትን ኪሳራ በ52.83 በመቶ መቀነስ መቻሉን አስታዉቆ ይህንን መሻሻል ያስመዘገበው በሀገሪቱ ከተተገበረው የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ እና በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ከታየው የጸጥታ መረጋጋት ጋር ተያይዞ መሆኑን ገልጾ እንደነበር ዪታወሳል።