Addis Standard Amharic – Telegram
Addis Standard Amharic
18K subscribers
4.75K photos
123 videos
3 files
3.78K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
ዜና: የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መሪዎች ጉብኝት፤ የሱዳን እና ሶማሊያ መሪዎች አስመራን ሲጎበኙ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ጁባን ጎብኝተዋል

ጉብኝቶቹ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ከሚያደርጉት ገብኝት አንድ ቀን ቀድሞ የተካሄደ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን ፈጥሯል። አንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ ቆይታቸው በቅርቡ በዋሽንግተን ተካሂዶ በነበረው የዩኤስ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ወቅት የተደረሱ ስምምነቶች ትግበራን ከህብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል።

ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በጁባ የነበራቸውን ቆይታ አስመልክተው በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ፌስቡክ እንዳሰፈሩት መልዕክት ከሆነ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን መረጋጋት እና ሰላም ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት አጋርተው ተመልሰዋል። የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ሳልቫ ኪር ከአብይ አህመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች በ2018 የተፈረመው የሰላም ስምምነት አተገባበር ዙሪያ መክረዋል ሲሉ ለጋዜጠኞች በጁባ ተናግረዋል።

ሌላኛው ትላንት የካቲት 4 ቀን 2015 አመሻሽ ላይ የተሰማው ጉብኝ ደግሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ማህሙድ በስምት ወራት ውስጥ ወደ አስመራ ያደረጉት ሶስተኛ ጉብኝት ነበር። የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አስመራ የተገኙት ለሁለት ቀናት ጉብኝት መሆኑን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር በድረገጹ አስነብቧል። ሁለቱም መሪዎች የጋራ በሆኑ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ድረገጹ ጠቁሟል።

https://amharic.addisstandard.com/ዜና-የአፍሪካ-ቀንድ-ሀገራት-መሪዎች-ጉብኝ/?fbclid=IwAR0Fv-ANcUeCgez5awhL1BCK9xJ9-bOgOPkB3jBaWVOKS9mDPhM1fjS_eYk
የመከላከያ ሚኒስቴር በተለያዩ የ #ኢትዮጵያ ክፍሎች በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች 220 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

የገንዘብ ድጋፉን ለሚመለከተው አካል ያስረከቡት የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰውን ድርቅ ምክንያት በማድረግ መከላከያ ሰራዊቱ 220 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል ሲል የመከላከያ ሚኒስቴር ጨምሮ ገልጿል።

"መከላከያ ሰራዊታችን ከተረፈው ሳይሆን ካለው ላይ ቀንሶ ወገንን መደገፍ እና መርዳታ አብሮት የመጣ እሴቱ" መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታዋ መከላከያ ሰራዊቱ ያሰባሰበዉን 220 ሚሊዮን ብር በ #ኦሮሚያ ክልል ለ #ቦረና እና አካባቢዉ፤ ለ #ሱማሌ ከልል፤ በ #ደቡብ ክልል #ኦሞና #ሰገን አካባቢዎች እንዲሁም በ #አማራ ክልል ለ #ዋግ አካባቢ ድጋፍ የሚዉል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዜና: #ሳዑዲአረብያ ዜጎቿ #ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችን እንዲቀጥሩ ከሶስት አመታት በኋላ ፈቀደች፤ የተቀመጠው የክፍያ ጣሪያ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል

የሳዑዲ አረብያ መንግስት ዜጎቹ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችን እንዲቀጥሩ ከሶስት አመታት በኋላ መፍቀዱን ይፋ አደረገ። በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የቤት ሰራተኛ የሚመለምሉ ድርጅቶች ኢትዮጵያውያንን ሲቀጥሩ ቅጥሩን የሚፈጽሙትን የክፍያ ጣሪያም አስቀምጧል። በተቀመጠው የክፍያ ጣሪያ መሰረትም አንዲት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ በሳዑዲ አረብያ የምታገኘው ከፍተኛ ክፍያ 6900 የሀገሪቱ ገንዘብ ሪያል ወይንም 1840 የአሜሪካ ዶላር የማይበልጥ መሆኑም ተገልጿል። ክፍያው ተጨማሪ እሴት ታክስ ወይንም ቫት ሳይጨምር መሆኑም ተመላክቷል።

የሳዑዲ አረብያ የሰው ሃብት እና ማህበራዊ ልማት ሚኒስትር እንዳስታወቀው በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የቤት ሰራተኛ መልማይ ኤጀንሲዎች እና ተቋማት ከተቀመጠው የክፍያ ጣሪያ በላይ ክፍያ እንዳይፈጽሙ አስጠንቅቋል።

https://amharic.addisstandard.com/ዜና-ሳዑዲ-አረብያ-ዜጎቿ-ኢትዮጵያውያን-የ/
ዜና: የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት አንድ ግዜ ከአዲስ አበባ ወደ ኮፐን ሀገን የጭነት በረራ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6/ 2015 ዓ.ም - የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት አንድ ግዜ ከአዲስ አበባ ወደ ኮፐን ሃገን የጭነት በረራ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ። ከመጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደው ሳምንታዊ በረራ 45 ቶን የመጫን አቅም ያለው B767-300F የካርጎ ፕሌን መጠቀሙን ገልጿል። አዲሱ የጭነት በረራው በአውሮፓ እና በተቀረው አለም ያለውን የንግድ ትስስር ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አስታውቋል።

ከጭነት በረራው በተጨማሪ ወደ ኮፐንሀገብ የሚያደርገውን ሳምንታዊ መንገደኛ የማጓጓዝ በረራ ከግንቦት ወር ጀምሮ ወደ አምስት እንደሚያሳድገው ጠቁሟል።

https://amharic.addisstandard.com/ዜና-የኢትዮጵያ-አየር-መንገድ-በሳምንት-አ/?fbclid=IwAR07Rp_JPWLbfBOHX03kayg9oBdOiVjodWjVTx_2hAqCmIAvzxhF6elbkZc
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 6ኛው ክልል አቀፍ የባህል እና ዋዛ ፌስቲቫል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ጀመረ

#ቤኒሻንጉልጉሙዝ ክልል 6ኛው ክልል አቀፍ የባህል እና ዋዛ ፌስቲቫል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ጀመረ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ኮሙኒኬሽን ቢሮ እንደገለጸው፣ "ባህላችን ለአብሮነታችንና ለዘላቂ ሰላማችን" በሚል መሪ-ቃል መከበር የጀመረው ፌስቲቫል በባህላዊ ሁነቶች፣ በፓናል ውይይት፣ በኤግዚቪሽንና ባዛር በድምቀት ይከበራል።

"ፌስቲቫሉ በዛሬው ዕለት በፓናል ውይይት መከበር የጀመረ ሲሆን፣ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል" ሲልም ቢሮው ጨምሮ ገልጿል።

በመድረኩም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሠር አበባው አያሌውን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዜና ትንታኔ: #አዲስ አበባን የሁከት ማእከል ለማድረግ የተደረጉ ሙከራዎች መክሸፋቸውን ከንቲባ #አዳነች አበቤ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6/ 2015 ዓ.ም - አዲስ አበባ ከተማን የሁከት ማእከል ለማድረግ በተለያየ ግዜ የተደረጉ የተለያዩ ሙከራዎች መክሸፋቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አበቤ አስታወቁ፡፡

ከንቲባዋ በመካሄድ ላይ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤው ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት ባለፉት ስድስት ወራት የከተማ አስተዳደሩ ካስመዘገባቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ከተማይቱ የሁከት አውድማ ከመሆን ለመታደግ የተሰራ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፉት ወራት መነሻቸውን ከአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎቸ ያደረጉ ተጓዦች በኦሮምያ ክልል የጸጥታ ሀይሎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከላቸውን የተመለከተ ዘገባ የክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ አሚኮ ማሰራጨቱ ይታወሳል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (#አብን) ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከንቲባዋ ያቀረቡት ሪፖርት ተቃውሞ መንግስት ከንቲባዋን ከስልጣን እንዲያነሳ እና ለፍርድ እንዲያቀርብ አሳስቧል።

ከሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ መግባት ከአማራ ክልል ነዋሪዎች አስቸጋሪ ሁኗል በሚል ከክልል ምክር ቤት አባላት ለቀረበ ጥያቄ የክልሉ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ሲመልሱ ዜጎች በሀገራቸው በነጻ መንቀሳቀስ አለባቸው ይህም በህገመንግስቱ ተደንግጓል፤ ይህን ማስከበር አለብን ማለታቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም #ሱዳን በነጻ እየገባን አንዳንድ ሀገሮች ላይ ያለቪዛ በቀጥታ እየገባን በሀገራቸው እዚህ ቁሙ ሊንባል አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል።

https://amharic.addisstandard.com/ዜና-አዲስ-አበባን-የሁከት-ማእከል-ለማድረ/
#ኢትዮጵያ እና #አሜሪካ ግንኙነታቸውን "ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ" ተስማሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ረፋድ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንን ተቀብለው አነጋግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፅህፈት ቤት እንደገለው፣ ውይይታቸው በተለያዩ የሀገር ውስጥ፣ ቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማምተዋል።

"ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነቱ ላይ እያስመዘገበች ያለችው ስኬት ተቀባይነት አግኝቷል" ያለው ፅህፈት ቤት "በኢኮኖሚው፣ በልማት ጥረቶች፣ በተለይም በግብርና እና በቀጣናዊ መረጋጋት ላይ ያሉ ጉዳዮችም ትኩረት ተሰጥቶባቸዋል" በማለት ጨምሮ ገልጿል።
ዜና: የ #ኢትዮጲያ ቀይ መስቀል ማህበር ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በ #ቦረና እና በ #ሞያሌ አካባቢዎች 28 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ

*በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎችም ቀጣይነት እንዲኖራቸው ስልታዊ እና የተቀናጁ መሆን እነዳለባቸው ማህበሩ አሳስቧል፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ቶላ በቦረና ዞን በድርቅ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው አባባቢዎች በሁሉም አቅጣጫ ማለትም በውሀ አቅርቦት፣ የተረፉትን ከብቶች በማከምም ሆነ ህብረተሰቡ ወደ ተለመደ ያኗኗር ዘይቤው እንዲመለስ እና ቀጣይ ህይወቱን እንዲመራ ዘር በማቅረብም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ እና ጤናን መሰረት ባደረጉ ድጋፎች በቅንጅት መስራት እነዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ህብረተሰቡ በማህበራዊ፣በስነልቦናም ሆነ በኢኮኖሚ በመጎዳቱ ከምግብ እና ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የስነ-ልቦና፣ የጤና እና ወደተለመደ ሕይወቱም በቀላሉ እንዲመለስ ጥብቅ የሆነ ክትትል እንደሚያስፈልገው የኢትዮጲያ ቀይ መስቀል ማህበር የወጣት በጎፈቃደኞች ተወካይ የቦርድ አባል ዶ/ር አዲስአለም ሙላት አሳስባለች፡፡

https://amharic.addisstandard.com/ዜና-የትዮጲያ-ቀይ-መስቀል-ማህበር-ባለፉት/?fbclid=IwAR1GqaOjHgImIstr-jBzEr_iL9miF7L4RJPAtbJCTGNISKJO0kqHaCcTZ0k
ዜና: #የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሦስት እና አራት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለውን እግድ እንዲያነሳ #ኢሰመኮ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7/2015 ዓ.ም - አዲስ አበባ የከተማ አስተዳደሩ ባለሦስት እና አራት እግር (ባጃጅ) አነስተኛ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተሽከርካሪዎች ላይ ያስቀመጠውን ሙሉ እገዳ በማንሳት ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊያመቻች ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠይቋል። በሁሉም የከተማዋ ክፍሎች ላልተወሰነ ጊዜ ገደብ መጣሉ ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገላቸው መብቶች አደጋ ላይ የጣለ እርምጃ ነው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።

ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል እገዳው በከተማዋ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ በመሆኑ የባጃጅ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎቹንና ቤተሰባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በርካታ ተጠቃሚዎችንም ችግር ላይ እንደጣለ መረዳቱን ያመላከተው የኮሚሽኑ መግለጫ መንግሥት ሰዎች ሥራቸውን እና የመረጡትን መተዳደሪያ ያለአግባብ እንዳያጡ ማድረግን ጨምሮ የመረጡትን እና የተቀበሉትን ሥራ እንዲሠሩ የማስቻል ኃላፊነት አለበት ሲል አሳስቧል።

ኮሚሽኑ እገዳውን ተከትሎ የደረሱትን አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችን ማነጋገሩን በመግለጫው አስታውቆ ኃላፊዎቹ በከተማዋ ወደ #10 ሺህ የሚገመቱ “የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ፈቃድ ያልተሰጣቸው መሆኑን፣ እንደ አንድ አገልግሎት ሰጪ በከተማዋ አሠራር ሥርዓት ያልተዘረጋላቸው መሆኑን፣ እንዲሁም ሌሎችም ተዛማጅ ችግሮች” መኖራቸውን እንደገለጹለት አመላክቷል።

https://amharic.addisstandard.com/ዜና-የአዲስ-አበባ-ከተማ-አስተዳደር-ባለሦ/?fbclid=IwAR0KaHrFqm5WXn_43hYyN7rNH_d4SEV6M2gmEqnxzfT1HxaafMQoyDSqSqs
ዜና: #በኢትዮጵያ ጦርነቱ ያደረሰውን ጉዳት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ #ብሊንከን በጥንቃቄ ሲመልሱ በሰላም ስምምነቱ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7/ 2015 ዓ.ም - ትላንት ረቡዕ መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት #የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጥንቃቄ በተሞላበት፣ ላለማስቀየም ጥረት በታከለበት መንገድ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት በተካሄደው ጦርነት የተፈጸመውን ግፍ እና ጥፋት አስመልክተው ምላሽ ሰጥተዋል። ትኩረት ማስቀየሻ በሚመስል መልኩ አጽንኦት ሰጥተው #ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኋላ ግፉ እና ጥፋቱ መቀነሱ ላይ አተኩረዋል። በተጨማሪም የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት ሁለቱም አካላት፣ #ፌደራል መንግስቱ እና #የህወሓት ሀይሎች የተፈጸመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ያስከተለውን ጉዳት አምነዋል፣ ተቀብለዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት #በትግራይ የተፈጸመውን ከጦርነት ጋር የተያያዘ ሰብአዊ መብት ጥሰት የዘር ፍጅት ወይንም ጀኖሳይድ መሆኑን የሚያትተውን በ2021 የተደረሰውን ሪፖርት መደርደሪያው ላይ እንዲቀመጥ እና እንዳይቀርብ አድርጎታል ሲል ብሊንከን ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ #ፎሬን ፖሊሲ መጽሔት ይፋ አድርጓል። ይህንንም ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሶስት ዲፕሎማት መስማቱን መጽሔቱ በዘገባው አስታውቋል።

#አዲስ ስታንዳርድ ብሊንከን በአዲስ አበባ #ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገኝቶ ይህንኑ ጉዳይ ጠይቋቸው ነበር፤ ለምን ሪፖርቱ ይፋ አልተደረገም? ሲል። ጥያቄውን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ በጦርነቱ ወቅት በንጹሃን ላይ የተፈጸሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሀገራችው በተደጋጋሚ በግልጽ ስትኮንን እንደነበር እና በሁሉም ጎራ ያሉ ጥቃቱን የፈጸሙ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማቅረቧን አውስተው ይህንን ጉዳይ ከአንድ አመት በፊት እኔ እራሴ ገልጨው ነበር ብለዋል።

https://amharic.addisstandard.com/ዜና-በኢትዮጵያ-ጦርነቱ-ያደረሰውን-ጉዳት/?fbclid=IwAR2Xx9qTDDo7cYc5PX9R8uigJDUUIXSycdPpqNgWVzVOP6Q7U-7JEOd_Eu4
#አማራ ባንክ #መርሀባ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን መጋቢት 9 በይፋ የሚመረቅ መኾኑን ገለጸ

የአማራ ባንክ መርሀባ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን መጋቢት 9 በይፋ የሚመረቅ መኾኑን ገልጿል።

ባንኩ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት በተለያዩ የአገልግሎት አማራጮች ለደንበኞቹ ቅርብ በመኾን ላይ መኾኑን ተገልጿል። በአፍሪካ መሪ እና ጨዋታ ቀያሪ እንዲሁም ተወዳዳሪ የመኾን አላማን አንግቦ መነሳቱን ባንኩ ገልጿል።

እስካሁን በተጓዘባቸው መንገዶች ከፍተኛ የካፒታል አቅምን በማጎልበት ተወዳዳሪ ለመኾን የሚያስችል ቁመና በመገንባት ላይ ሲሆን ተወዳዳሪ ለመኾንና አላማውን ለማሳካት ቀልጣፋ፣ በሁሉም ተደራሽ ፣ ጊዜውን ያማከለ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል ተብሏል።

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በባንክ ወለድ ምክንያት ከባንክ የራቁ ደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት በወለድ ከሚሰጡት መደበኛ የባንክ አገልግሎት በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ በከፍተኛ ኹኔታ በማስፋት እና በማደግ ላይ እንደሚግርኝ ባንኩ ገልጿል ።

ባንኩ በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የመደበኛ የባንክ አገልግሎት በሚሰጡ ከ230 ቅርንጫፎች በላይ በመስኮት በኩል የተሟላ የመርሀባ ከወለድ ነፃ የባንክ አገለግሎት በመስጠት ላይ መገኘቱን ባንኩ አመላክቷል።

እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 30 ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መኾኑን ባንኩ ገልጿል።

https://www.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid02HWzstL2BYijczMBUPFrpka5ovx8PBo9ATYzJhtbvoYqdmZKt5mJdbbmSdp5rGYF1l
በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ47 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን በቁጥጥር ስር ዋለ

መነሻውን #ጅቡቲ ያደረገ የነዳጅ ማመላለሻ ቦቲ ከተመደበለት መዳረሻ ውጪ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው 47 ሺህ ሊትር ቤንዚን በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

የአዲስ አበባ #ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ክትትል ተሽከርካሪው ስምሪት ከተሰጠው ቦታ ውጪ ወደ ደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በመጓዝ ላይ እያለ #ሞጆ ከተማ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ይህን ህገወጥ ድርጊት የፈጸመው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን የተያዘው ቤንዚንም በነዳጅ አቅራቢው ድርጅት ማደያ ተራግፏል፡፡

የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ኢ.ፕ.ድ
#አዲስአበባ የኃይል መቆራረጥ በውሃ ምርት እና ስርጭት ላይ ችግር እንደፈጠረበት የከተማዋ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን ገለጸ

ከመጋቢት 1 ቀን 2015ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ስምንት ቀናት በባለሥልጣኑ የውሃ ጉድጓዶች እና የግፊት ጣቢያዎች ላይ በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ማጋጠሙን በባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሠርካለም ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

ይህም በባለስልጣኑ የውሃ ምርት እና ስርጭት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ነው ዳይሬክተሯ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡

በኃይል መቆራረጡ ምክንያት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣ 2፣3፣ 5፣ 12፣ 13 እና 14፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣2፣3፣4፣5፣6 እና 10 እንዲሁም በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2፣3፣4፣5፣6፣9፣10፣11፣12፣13 እና 14 የውሃ አቅርቦቱ ተቋርጧል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣9 እና 10፤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 1 እስከ 13፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 1 እስከ 6 እና ከወረዳ 9 እስከ 11 የውሃ አቅርቦቱ መቋረጡን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 1 እስከ 15፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣ 2፣ 11 እና 12፤ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 እና 5 በከፊል እና ወረዳ 9 በሙሉ እንዲሁም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የውሃ አገልግሎቱ መቋረጡን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

https://www.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid02Zzv31WrbQaDLESbRttmrHHyK3uRjY9WyDcLcGCto85vcAnmfVN5ZM6oWwnT7oKUul