Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/ – Telegram
Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25.9K subscribers
40K photos
303 videos
7 files
5.75K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
የኢፕድ ስልጠና ማዕከል ከሰባት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት አመራሮችና ሰራተኞች የሚሰጠውን ስልጠና ጀመረ
*****
(ኢ ፕ ድ)
ለፌዴራልና ለከተማ አስተዳደር ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ተከታታይ ስልጠናዎችን እየሰጠ ያለው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) ስልጠና ማዕከል፤ ከሰባት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት አመራሮች እና ሰራተኞች የሚሰጠውን ስልጠና ዛሬ ጀምሯል።

ለድርጅቱ አመራሮችና ሰራተኞች "መልካም ስብዕና ግንባታ ለአገልጋይነት አስተሳሰብና ተግባር" የሚሰጠው ስልጠና በአምስት ዙር የሚከናወን ሲሆን፤ ዛሬ በተጀመረው በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ከ800 በላይ አመራሮች እና ሰራተኞች ተካፋይ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው አለሙ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ድርጅታችን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በቀን ያገለግላል። ይህም ማለት የድርጅቱ ሠራተኞች በቀን ከበርካታ ሰዎች ጋር ተግባቦት ያደርጋሉ ማለት ነው።

ስለዚህ የተገልጋይን አመለካከት በመገንዘብ ቀልጣፋ አገልገሎት መስጠት ያስፈልጋል። ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከር ኢፕድ ስልጠና እንዲሰጠን ወስነናልዕ ብለዋል።

ኢፕድ አንጋፋ እና ትልቅ የሚዲያ ተቋም እንዲሁም በስልጠና ዙሪያ በቂ ልምድ ያለው ተቋም በመሆኑ ለአምስት ቀናት ከሰባት ሺህ በላይ አመራሮች እና ሰራተኞች የሚሰጠው ስልጠና በስራቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደሚያምኑ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፤ ኢፕድ ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት ጋር በጋራ በመስራቱ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ኢፕድ "መልካም ስብዕና ግንባታ ለአገልጋይነት አስተሳሰብና ተግባር" በሚል ጽንሰ ሀሳብ የሚሰጠው ስልጠና ከድርጅቱ የእለት ተዕለት ስራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

ኢፕድ በአዲስ አበባ የአውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ያለውን ሁኔታ የሚሳዩ ታሪካዊ ፎቶዎች፣ ዜናዎች እና በርካታ ጽሑፎች ዶክመንተ አድርጎ መያዙን ጠቁመው፤ ይህንን የድርጅቱን ታሪክ በፎቶ ቡክ፣ በመጽሔት እና በዶክመንተሪ ለመያዝ በሚፈልግበት ወቅት ኢፕድ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢፕድ ስልጠና ማዕከል በሳለፍነው እና በዚህ ሳምንት በተከታታይ ለአስር ተቋማት በ14 ርዕሶች ላይ ለፌዴራልና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ስልጠናዎችን መስጠቱ ይታወሳል።

በሳሙኤል ወንድወሰን
በትግራይ ክልል ሁለት ዞኖች አርሶ አደሮች ጤፍን በኩታ ገጠም ለማልማት እየሰሩ ነው
**********************
(ኢ ፕ ድ)

በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ እና ማዕከላዊ ዞኖች አርሶ አደሮች ጤፍን በኩታ ገጠም የማልማት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኝ የክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል አስታወቀ።

በማዕከሉ የጤፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ኃይሉ ለኢዜአ አንደገለጹት በሁለቱም ዞኖች 50 ሺህ አርሶ አደሮችን ወደ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ለማሸጋገር በ850 የጤፍ ክላስተር ተደራጅተው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።

አርሶ አደሮቹ ጤፍን በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለማልማት እስካሁን ባደረጉት እንቅስቃሴ 12 ሺህ 750 ሄክታር ማሳ በጤፍ ምርጥ ዘር እየሸፈኑ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ አርሶ አደሮቹ ማሳቸውን በእርሻ ትራክተር ማረስ መቻላቸው በበሬ ለማረስ እና አረም ለማረም የማያባክኑት የነበረውን ጊዜና ጉልበት ለሌሎች የልማት ስራዎች እንዲያወሉ ያስችላቸዋል።

በኩታ ገጠም ተደራጅተው እርሻቸው አዘምነው መስራት መጀመራቸው ምርታማነትን አሳድገው የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፈው ምርት ለገበያ አቅርበው ገቢያቸውን ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው አመልክተዋል።

አርሶ አደሮቹ ግብርናን በዘመናዊ መንገድ ማከናወን እንዲችሉ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲቲዩት የበጀት ድጋፍ እንዳደረገላቸውም ነው አቶ ቴዎድሮስ የገለጹት።

በማዕከሉ በኩል በስድስት ወረዳዎች ለሚገኙ የአቅም ውስንነት ላለባቸው ሴት አርሶ አደሮች ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በትራክተር የማረስ ስራ እየተከናወነ እና ማዕከሉ የጤፍ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ከሁለገብ የሕብረት ስራ ዩኒየኖች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሀፀቦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስዩም ዓለማየሁ በበኩላቸው ግብርናን በእርሻ ትራክተር ማረስ በባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ጉልበትና ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስቀርላቸው ገልጸዋል።

አርሶ አደር ብርሃኑ ታከለ የእርሻ ትራክተር ተጠቅመው ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን መተግበር የአፈር ለምነት ጠብቆ በሰብል ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን እና አረምን ይቀንሳል ብለዋል።
የከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት‼️
“ነገን ዛሬ እንትከል” በሚለዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውብ የተፈጥሮ ገጽታ ባላት የጌዲኦ ዞን ችግኝ በመትከል አሻራችንን አኑረናል። የጌዲኦ ህዝብና አባገዳዎች ላደረጋችሁልን ደማቅ አቀባበል እናመሰግናለን።
ከ141 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
**********
(ኢ ፕ ድ)

የጉምሩክ ኮሚሽን ከሰኔ 2 እስከ 8/ 2015 ባደረገው ክትትል 76 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ የወጭ፤ በድምሩ 141 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን በዚህም ጅግጅጋ ፣ ሞያሌ እና አዋሽ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በቅደም ተከተላቸው 21 ሚሊዮን፣ 18 ሚሊዮን እና 11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ወስደዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋዉሩ የተገኙ ስድስት ግለሰቦች እና አራት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝባችን ምስጋናውን ያደርሳል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን ያቀርባል፡፡