Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/ – Telegram
Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25.9K subscribers
39.9K photos
298 videos
7 files
5.74K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
የሕፃናት የላንቃና ከንፈር መሰንጠቅ ችግር የመበራከቱን ያህል ሕክምናው አልተዳረሰም
*****************
(ኢ.ፕ.ድ)
- አለርት ሆስፒታል ከ100 በላይ ለሆኑ ሕጻናት ህክምና ሰጥቷል

የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ሕፃናት የመብዛታቸውን ያህል የሕክምናው ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑን የአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ዶክተር አታክልቲ ባራኪ አስታወቁ።

አለርት ሆስፒታል ከ100 በላይ ለሚሆኑ ሕፃናት የላንቃ እና ከንፈር ቀዶ ሕክምና ሰጥቷል።
ዶክተር አታክልቲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 20 ሚሊዮን ብር የወጣበት የሕፃናት የላንቃ እና የከንፈር መሰንጠቅ የቀዶ ሕክምና መስጫ ማዕከል ካስመረቀ ስድስት ወራት ተቆጥረዋል።

በዚህም ዕድሜያቸው ከሰባት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ባለፉት ስድስት ወራት በማዕከሉ የቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸዋል።

በቁጥር ከአንድ መቶ በላይ ሕፃናት በማዕከሉ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸዋል ያሉት ዶክተር አታክልቲ፤ በሀገር ደረጃ የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ ነው። ነገር ግን የቁጥሩን ያህል ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች የሚታዩ ቢሆንም አሁንም በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ ብለዋል።

ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ሆስፒታሉ ከአጋር አካላት ጋር እየሠራ ነው። በዚህም አጋር አካላት ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ወደ ማዕከሉ ይዘው ይመጣሉ።

በሂደቱም በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ ያሉት ዶክተር አታክልቲ፤ በአብዛኛው የሕፃናቱ ወላጆች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው መሆኑ እና ስለሕክምናው በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ ሕፃናቱ የአመጋገብ እና የመጥባት ችግር እንዲያጋጥማቸው ያደርጋል ብለዋል።

ይህም ችግሩ ያለባቸው ሕፃናት በኢንፌክሽንና ሌሎች መሰል ችግሮች እንዲሰቃዩ እንደሚያደርግ እና ባስ ሲልም ከነዚህ ችግሮች ጋር በተያያዘ አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ሕይወታቸው እንደሚያልፍ አስረድተዋል።

የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ችግርን በቀላል ቀዶ ሕክምና በመቅረፍ የሕፃናቱን ሕይወት ማስተካከል ይቻላል ያሉት ዶክተር አታክልቲ፤ ስለዚህ ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ የአጋር ድርጅቶችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህን ቀላል ቀዶ ሕክምና ተደራሽ በማድረግ የሕፃናት ሕይወት እንዳይጎዳ፤ የመናገር፣ የመስማትና ሌሎች የሥነ ልቦና ችግሮች እንዳይደርሱባቸው የአለርት ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕፃናት የላንቃ እና የከንፈር መሰንጠቅ የቀዶ ሕክምና መስጫ ማዕከል ማቋቋሙን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በማዕከሉ የቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው ሁለትና ሦስት ዓመት የሞላቸው ሕፃናት ናቸው ያሉት ባለሙያው፤ ወላጆች በሕክምና ተቋማት እንዲወልዱ በማድረግ ሕፃናቱ ስድስት ወር ሲሞላቸው ሕክምና እንዲደረግላቸው እየተሞከረ ነው። ይህም በልጆች ላይ የሚደርሰውን አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት ይቀንሳል ሲሉ ገልጸዋል።

በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም
600 ሺህ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ቦሮን ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ትላንት ወደብ ደርሳለች
*************
(ኢ.ፕ.ድ)

-እስከ ሐምሌ 23/2015 ድረስ ከሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ተጨማሪ ማዳበሪያ ከውጭ እንደሚጓጓዝ ይጠበቃል

-ከውጭ የተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ከ10 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ደረሰ

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለ2015/16 የሰብል ዘመን ከገዛው 15 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ሐምሌ 3/2015 ዓ.ም. ድረስ 10 ሚሊዮን 275 ሺህ 320 ኩንታል ከውጭ መጓጓዙን የግርና ሥራዎች ኮርፓሬሽን አስታወቀ።

ትላንት ሐምሌ 2/2015 ዓ.ም. 600 ሺህ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ቦሮን ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ጂቡቲ ወደብ መድረሷንም አስታውቋል።

ወደብ ከደረሰው አጠቃላይ ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 8 ሚሊዮን 487 ሺህ 429 ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደር ዩኒየኖች እየተሰራጨ ይገኛል።

እስከ ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም. ድረስ ተጨማሪ 3 ሚሊዮን 685 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ከውጭ እንደሚጓጓዝ ይጠበቃል ተብሏል።

ከዚህ መጠን ውስጥ ሁለት ሚሊዮን 485 ሺህ ኩንታል ዩሪያ ሲሆን፣ ቀሪው 600 ሺህ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ እና 600 ሺህ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ቦሮን ናቸው።

ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም
"ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ቃል የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ለማሻሻል የተዘጋጀ ንቅናቄ በሀዋሳ ተካሄደ
***************
(ኢ.ፕ.ድ)

"ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ቃል የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ለማሻሻል የተዘጋጀ የትምህርት ተሃድሶ ንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ ተካሄደ።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ የንቅናቄ መርሃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፤ ብቁና ተወዳዳሪ ትዉልድ ለማፍራት ጥራት ያለዉ ትምህርት ለዜጎች ማድረስ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራት ለማስፈን ከአምና ጀምሮ በክልል ደረጃ ንቅናቄ መጀመሩን ያስታወሱት ፕሬዘዳንቱ: ባለፉት ሃያ ቀናት በክልሉ በትምህርት ተሐድሶ የተሰሩ ስራወችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውንና ያለቁ ትምህርት ቤቶችን ማስመረቀቸውንም ገልፀዋል።

በዚህም ተስፋ ሰጪ ዉጤቶች መመዝገባቸውን ለመመልከት ችለናል ሲሉም ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት አመት አንድ መቶ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ 83 ትምህርት ቤቶች ተገንብተው እንደተመረቁና ቀሪዎቹ በተለያየ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አቶ ደስታ ገልጸዋል።

አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ የገጠር አከባቢ ነዋሪ በመሆኑና በገጠሩ አከባቢ የትምህርት ተደራሽነትና የጥራት ዉስንነት በመኖሩ ብቁ ዜጋን በማፍራት በኩል ክፍተቶች እንደነበሩ የተናግረው፣ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተስራ መሆኑን ገልጸዋል።


በአዲሱ አዶላ (ሀዋሳ)
ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢጋድ የሱዳንን ግጭት ለመፍታት ያቋቋመውን የአራትዮሽ የመሪዎች ጉባኤን ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ ማስተናገዳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል ::
በክልሉ ካሉ ትምህርት ቤቶች መስፈርቱን የሚያሟሉት 29ኙ ብቻ ናቸው
*****************
(ኢ ፕ ድ)
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካሉ 643 የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ተቋምነት መስፈርትን የሚያሟሉት 29ኙ ብቻ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ አጠቃላይ ትምህርት ጥራት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ሉሌ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በክልሉ ጥናት ከተደረገባቸው 643 የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተቀመጠውን ደረጃ የሚያሟሉት 29ኙ ብቻ ናቸው።

ትምህርት ቤቶቹ ደረጃ የተቀመጠላቸው ባሟሉት ግብአት፣ በመሠረተ ልማታቸውና ተማሪዎች ባስመዘገቡት ውጤት ተመዝነው መሆኑን ገልጸው ፤ በዚህም ከ601 የመጀመሪያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 572ቱ ደረጃ የወጣላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ደረጃ ከወጣላቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ 143 ቱ ከ50 በመቶ በታች ውጤት ያላቸው በመሆኑ ደረጃ አንድ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶችም ከፍተኛ የሚባል የትምህርት መሠረተ ልማት ችግር ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

403 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ደረጃ ሁለት ላይ የተቀመጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ደረጃውን ለማሟላት በሂደት ላይ በመሆናቸው መስፈርቱን ከሃምሳ እስከ 70 በመቶ ድረስ አሟልተዋል ነው ያሉት።

አቶ ዮሐንስ አንድ ትምህርት ቤት መስፈርቱን አሟላ የሚባለው ደረጃ ሦስት ላይ ሲደርስ መሆኑን አመልክተው፤ በክልሉም ካሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 26ቱ ብቻ ደረጃ ሦስት ላይ መቀመጣቸውን ገልጸዋል። ሆኖም አንድም ትምህርት ቤት ደረጃ 4 ላይ አለመድረሱን አስታውቀዋል።

በክልሉ ካሉ 92 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 73ቱ ደረጃ የወጣላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ከእነዚህ ውስጥም 15 ትምህርት ቤቶች ደረጃውን ሳያሟሉ ቀርተው ደረጃ አንድ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ዮሐንስ 55 የሚሆኑት ደግሞ ደረጃ ሁለትን ለማሟላት እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን፣ ደረጃቸውን አሟልተው ደረጃ 3 ላይ የተቀመጡት ትምህርት ቤቶች 3 ብቻ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ደረጃ አራት የገባ ትምህርት ቤት አለመኖሩን ጨምረው ገልጸዋል።

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጻ፤ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች የግብአት ችግር ያለባቸው ናቸው። ይህም የሆነው በፊት የነበረው የትምህርት ሥርዓት ከጥራት ይልቅ ተደራሽነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ነው።

አቶ ዮሐንስ የትምህርት ቤቶች ደረጃ እንደ ሀገር ችግር ያለበት ቢሆንም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ጠቅሰዋል።

ይህንን ለማስተካከል የክልሉ ትምህርት ቢሮ የራሱን ጥረት እያደረገ ነው። በተጠናው ጥናት መሠረትም በትምህርት ቤቶች የሚፈለገውን መሠረተ ልማት ለማሟላት ማስተካከያ እንዲደረግ ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ እንደ ሀገር የተጀመረው የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻል ንቅናቄ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓም