Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/ – Telegram
Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25.9K subscribers
39.9K photos
298 videos
7 files
5.74K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ደረሰ
++++++++++++++++++++++++++++

#ጋዜጣ_ፕላስ | በስርቆትና ውድመት የተነሳ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት እና የኃይል ስርቆት ላይ የደረሰበትን ጉዳት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር፤ ባለፉት አራት ወራት በመሰረተ ልማት በተፈጸመ ስርቆት፣ በመኪና አደጋ በደረሰ ውድመት እና በኃይል ስርቆት በድምሩ 114 ሚሊዮን 299 ሺህ 93 ብር የሚገመት ጉዳት በተቋሙ ላይ ደርሷል ብለዋል።

በ17 ትራንስፎርመሮች ላይ በተፈጸመ ስርቆት 23 ሚሊዮን 85 ሺህ 847 ብር ኪሳራ ደርሷል ያሉት ኃላፊው፤ በኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ ኬብል ስርቆት ደግሞ 88 ሚሊዮን 849 ሺህ 858 ብር ጉዳት ደርሷል ሲሉ ገልጸዋል።

በመኪና ግጭት የደረሰ የመሠረተ ልማት ውድመት ብዛት 15 ሲሆን፣ በብር ሲተመን 18 ሚሊዮን 178 ሺህ 731 ብር ጉዳት ማጋጠሙን አብራርተዋል።

ተቋሙ ባለፉት አራት ወራት 36 ነጥብ 45 ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት መፈጸሙን ጠቁመው፤ በዚህም ምክንያት ተቋሙ 13 ሚሊዮን 184 ሺህ 677 ብር አጥቷል ሲሉ አብራርተዋል።

በአጠቃላይ ባለፉት አራት ወራት 107 ጉዳቶች እንደተመዘገቡ ጠቅሰው፤ 10 የወንጀል ክሶች ተመስርተው በፍርድ ሂደት ላይ እንደሚገኙ፣ ቀሪዎቹም በፖሊስ የምርመራ ሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በታደሠ ብናልፈው
#ጋዜጣ_ፕላስ #ኤሌክትሪክ #መሠረተልማት #ኢትዮጵያ
4🤔1
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከባንክ ስርዓት ጋር የማጣመር ሥራ ተጀመረ
+++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከባንክ ስርዓት ጋር የማጣመር ሥራን ዛሬ በጋራ ማስጀመራቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቁ።

የፋይናንስ ዘርፍ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ ምዕራፍ የሆነውን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከባንክ ስርዓት ጋር የማጣመር ሥራ በይፋ መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወጣው መግለጫ ገልጿል።
👍7🙏1
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የሰላም ስምምነቱ ድርጅታዊ ዕውቅና ያለው መሆኑን ገለጸ
++++++++++++++++++

#ጋዜጣ_ፕላስ | በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ድርጅታዊ ዕውቅና ያለው መሆኑን አፋህድ አስታውቋል።

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የፖለቲካ መምሪያ ምክትል ኃላፊ እያሱ አበራ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ድርጅታዊ ዕውቅና ያለው ነው።

የፈጸመው ስምምነት የአማራ ህዝብን ወደ ሰላም የሚመልስ መሆኑን ጠቁመው፤ ስምምነቱም በድርጅቱ አመራሮች እና ሠራዊት ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ህዝብን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ከመንግስት ጋር በመሆን ለመፍታት እንደሚሰራም ኃላፊው ተናግረዋል።

ሀገርን በሚያፈርስ ተግባር የተሰማሩ አካላት እየሄዱበት ያለው ሂደት ለማንም እንደማይጠቅም የገለጹት ኃላፊው፤ ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ አደረጃጀቶች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፈሕድ ጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ፋይናንስ ኃላፊ ከፈለ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የአማራ ህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ሲታገል መቆየቱን አውስተው፤ የተደረሰው ሰምምነት ህዝቡን ወደ ልማት የሚመልስ ነው ብለዋል።

የወሎ ቤተ አማራ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የህዝብ አስተዳደርና ማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ ግርማ እጅጋየሁ በበኩላቸው፤ የአፋሕድ የትጥቅ ትግል አካሄድ ለአማራ ህዝብ ጥቅም ባለማስገኘቱ ወደ ድርድር መመለሱን ጠቁመዋል።

በአማን ረሺድ
#ጋዜጣ_ፕላስ #አፋህድ #ሰላምስምምነት #አማራ
8😁1
የሶፍ ዑመር የባቡር መንገድ ግንባታ በተያዘው ዓመት ይጠናቀቃል
++++++++++++++++++++++++++

#ጋዜጣ_ፕላስ | በሶፍ ዑመር ዋሻና ሎጅ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለቱሪስት አገልግሎት መስጫ እየተገነባ የሚገኘው የባቡር መስመር በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ስለሺ ካሳ ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፤ የባሌ አካባቢን ቱሪዝም ለማሳደግ ሶፍ ዑመር ላይ እየተገነባ ያለው የባቡር መንገድ ግንባታ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል።

ኢትዮጵያ ከአሏት ዕምቅ ሀብቶች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው ያሉት ኢንጂነር ስለሺ፤ ሀገሪቱን ባላት የቱሪዝም ሀብት ልክ ተጠቃሚ ለማድረግ በትራንስፖርት ማስተሳሰር ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

በውስጥ አቅም በመገንባት የመጀመሪያ የሆነው ይህ ፕሮጀክት እስካሁን ከ50 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ገልጸው፣ አጠቃላይ ርዝመቱ አምስት ኪሎ ሜትር መሆኑን አስረድተዋል።

የባቡር መንገዱ በቀጣይም እንደ ሁኔታው ሊሰፋ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ጠቅሰው፤ ለጎብኝዎች ያለ ስጋት መንቀሳቀስ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

በሀገሪቱ በአጠቃላይ የባቡር መስመሮች ላይ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጂነር ስለሺ፤ አዋሽ - ኮምቦልቻ - ሀራ ገበያ የባቡር መንገድ ከዚህ በፊት የነበረውን የመሠረተ ልማት ስርቆት ችግር በመቅረፍ ከአማራና ከአፋር ክልሎች ጋር በተሰራ ስራ መቀነስ መቻሉን አያይዘው አመልክተዋል።

የባቡር መስመሩ አገልግሎቱን ለማስጀመር በውስጥ አቅም የመጠገን ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ በቅርቡም ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በልጅዓለም ፍቅሬ
#ጋዜጣ_ፕላስ #ባቡር #ሶፍ_ዑመር #ባሌ #ቱሪዝም
12
“ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው በባዳዎችና ባንዳዎች ዕኩይ ተግባር ነው”

- የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባል
++++++++++++++++++++++

#ጋዜጣ_ፕላስ | ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው በባዳዎችና ባንዳዎች ዕኩይ ተግባር ነው ሲሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባል ፒቲ ኦፊሰር ፈረደ ፍትሃነገስት ገለጹት።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባል ፒቲ ኦፊሰር ፈረደ ፍትሃነገስት ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው በባዳዎችና ባንዳዎች ዕኩይ ተግባር ነው።

ሉዓላዊ ሀገርን መዝጋት በራሱ በህግ አግባብ ተጠያቂ የሚያደርግ በመሆኑ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከህግ አግባብ ውጪ የሚሆንበት አንዳች ምክንያት የለም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሰብን ማጣት ያልነበረባት መሆኑን የጠቀሱት አባሉ፤ ያለፈውን መውቀስ ብቻ ሳይሆን ከነበረው ሁኔታ ትምህርት ተወስዶ ችግሮችን እያረሙ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለተፈጠረው ችግር ከቀድሞ ባህር ኃይሎች ምን ይጠበቃል የሚለውን ምላሽ ለመስጠት ማህበር ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አያይዘው እንደገለጹትም፤ ለ36 ዓመታት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ባህር ኃይል ማፍረስ በሀገር ላይ የተሰነዘረ ከባድ ጥቃት ነው።

በልጅዓለም ፍቅሬ
#ጋዜጣ_ፕላስ #ባህር_በር #ኢትዮጵያ #ቀይ_ባህር
6👍2
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአምባሳደር ባጫ ደበሌ የመጽሐፍ ምረቃ ላይ ከተናገሩት የተወሰደ‼️
4🤯1
“ስደተኛዋ” የጦር መርከብ
++++++++++++++

#ጋዜጣ_ፕላስ | በጦር ሜዳ ጀብድ ሠርታ፣ የሀገሪቱን ክብር በሚመጥን መልኩ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው መርከብ፣ ኃይለ ሥላሴ እናት መርከብ የሚል ስያሜ ተሰጥቷት ነበር።

በመናገሻነት በቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበች አገልግላለች።

ይህች መርከብ ታሪኳ በንጉስ ኃይለ ሥላሴ ይጀምርና መንግስቱ ኃይለ ማርያም ወደ ዚምባቢዌ ሲኮበልሉ የእርሷም እጣ ፋንታ ስደት ሆኖ ተቋጭቷል።

የቀድሞ ባህር ኃይል ባልደረባና ፎቶግራፈር አቶ ዳኜ አበራ፤ መርከቧ የኢትዮጵያ ስምና ኃያልነት የተጻፈባት ብዕር መሆኗን ይናገራል።

መርከቧ እ.ኤ.አ በ1962 ዓ.ም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ለንጉስ አጼ ኃይለ ሥላሴ በስጦታ የተሰጠች ነበረች።

ለኢትዮጵያ እስከተሰጠችበት ጊዜ ድረስ በአሜሪካ ባህር ኃይል ለበርካታ ዓመታት በማገልገል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተካፍላለች። ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ የነበራት Orca 49 ስያሜ ተቀይሮ HMS A01 ኃይለ ሥላሴ እናት መርከብ ተብላለች።

የጦር መርከቧ ከ100 ሜትር በላይ ቁመት ያላት ሲሆን፣ በውስጧ ቤተ መንግስት ተገንብቶላት ነበር። ከ250 በላይ መርከበኞችንና ሰልጣኞችን የመያዝ አቅም ነበራት።

በውስጧ የተሟላ መለስተኛ ክሊኒክና የመዝናኛ ስፍራ ያካተተች ነበረች፤ ጠላትን መከላከል የሚያስችሉ መሳሪያዎችንም ታጥቃ ነበር ይላል አቶ ዳኜ።

በደርግ ዘመነ መንግስት ስሟ ዳግም ተቀይሮ "A01 ጦር መርከብ ኢትዮጵያ" ተብላ እንድትጠራ ተደርጓል።

በ1970 ዓ.ም ሻዕቢያ ምፅዋን ለመያዝ በሞከረበት ወቅት የባህር ኃይል መርከበኞችና መርከቦች ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ የጦር መርከቧ አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር ዳኜ ይገልጻል።

በ1982 ዓ.ም ሻዕቢያ አጥፍቶ ጠፊ ጀልባዎችን ቢያሰማራም መርከቧ የጠላትን ጀልባ ዶግ አመድ ማድረግ ችላ ነበር።

በ1983 ዓ.ም ሻዕቢያ አሰብና አካባቢዋን በመቆጣጠሩ መርከቧ ወደ የመን ተሰድዳ ለረጅም ጊዜ ባህር ላይ ቆማ ጉዳት ደርሶባታል።

በመጨረሻም መርከቧ ጨረታ ወጥቶ በአሮጌ ላንድሮቨር ዋጋ የተሸጠች ሲሆን፤ ገዢው አካል ምንም ነገር ሳያስተርፍ ቆራርጦ እንደወሰዳት አብራርቷል።

መርከቧ በዓለም ውድ ከሆኑ ብረት የተሰራች መሆኗን የሚናገረው የቀድሞ ባህር ኃይል አባሉ፤ መርከቧ እንደሄደች የቀረችውም ሆነ በጨረታ የተሸጠችው መርከበኞቹ ቢጮሁም ሰሚ በማጣታቸው ነው ባይ ነው።

ዛሬ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ትንሣኤ መጀመሩ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለቀድሞ ባህር ኃይሎችም ትልቅ ስሜት ፈጥሯል በማለትም ደስታውን ይገልጻል።

በልጅዓለም ፍቅሬ
#ጋዜጣ_ፕላስ #ስደተኛዋ_መርከብ #ኢትዮጵያ_ባህር_ኃይል #ታሪክ #ቀይ_ባህር
11👍4