Addis Standard Amharic – Telegram
Addis Standard Amharic
18K subscribers
4.67K photos
121 videos
3 files
3.72K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
ዜና፡ ጋዜጠኛ #ተመስገን_ደሳለኝ በፌዴራል ፖሊስ አባላት ዛሬ ጠዋት ከመኖሪያ ቤቱ ተወሰደ
“ፍትሕ” መጽሔት መስራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፌዴራል ፖሊስ አባላት ዛሬ ጠዋት ከመኖሪያ ቤቱ መወሰዱን ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፀ፡፡
የፌዴራል ደምብ ልብስ የለበሱ እና ሲቪል የለበሱ በሁለት ፓትሮል የታጀቡ የፀጥታ አካላት ጠዋት 12፡ 30 ላይ ወደ መኖሪያ ቤቱ በማምራት ተመስገን ደሳለኝን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የገለፀው ወንድሙ ወዴት እንደተወሰደም የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ተናግሯል፡፡
https://rb.gy/tye7p
ዜና፡ #በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ #በሱዳን ጦር ሰራዊት እና አማጽያን መካከል ውጊያ መካሄዱ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው #የብሉናይል ግዛት #ኩርሙክ ከተማ በሱዳን ጦር ሰራዊት እና በአከባቢው በሚንቀሳቀሰው የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ ሰሜን በተሰኘ አማጺ ቡድን መካከል ትላንት ንጋት ላይ ውጊያ መካሄዱን ምንጮቹን ዋቡ በማድረግ ሮይተርስ የዜና ወኪል አስታወቀ።

በብሉ ናይል ግዛት የተነሳውን ውጊያ የሸሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአከባቢው ነዋሪዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን ዘገባው አካቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ ሱዳን ፖስት ይዞት በወጣው ዘገባ ግጭቱ የተጀመረው በሱዳን ከሚንቀሳቀሱ አማጺ ቡድኖች ውስጥ ትልቁ እንደሆነ የሚነገረው የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ ሰሜን በሱዳን ጦር ሰራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት በመፈጸሙ መሆኑን አመላክቷል።

https://rb.gy/s456m
ዜና፡ "ጥቂት አንቂዎች ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የ #አማራ ህዝብና #መንግስት እረፍት እንዳይኖራቸው በሃሰት መረጃ የጥፋት መንገድን በመከተል ላይ ይገኛሉ" - የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ

ጥቂት የሚባሉ አንቂዎች ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የአማራ ህዝብና መንግስት ማኀበራዊ እረፍት እንዳይኖራቸው በሃሰት መረጃ የጥፋት መንገድን በመከተል ላይ ይገኛሉ ሲል የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ይህን ያለው በአማራ ክልል ከትላንት ሰኔ 19 ጀምሮ ለሶስት ቀን ህዝባዊ ሰልፍ ይካሄዳል የሚል መረጃ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ ነው፡፡

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አንቂዎች ያላቸው አካላት የህዝብንና የመንግስትን ግንኙነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥሉ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ላይ በመጠመድ የአማራ ህዝብን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞ ወደ ኋላ የሚጎትት አሉታዊ ተግባር በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
https://rb.gy/4jhua
#ኢትዮጵያ: ኦዲት በተደረጉ 131 መስሪያ ቤቶች ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ መገኘቱን የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2014 በጀት ዓመት ሪፖርት አመላከተ።

እንደ ፓርላማው ዘገባ በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተ ኦዲት በተደረጉ 131 መስሪያ ቤቶች በጠቅላላው ከ15 ቢሊዮን 125 ሚሊዮን ብር በላይ ብር በወቅቱ ያልተወራረደና ያልተሰበሰበ ሂሳብ መኖሩ በኦዲት መረጋገጡን ዋና ኦዲር መሰረት ዳምጤ ገልጸዋል፡፡

"ጤና ሚኒስቴር፣ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና ትምህርት ሚኒስቴር በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት ተጠቃሽ መሆናቸውንም ዋና ኦዲተሯ በሪፖርታቸው አንስተዋል፡" በማለት ፓርላማው በተጨማሪ ዘግቧል።

ወይዘሮ መሰረት እንዳሉት ተሰብሳቢ ሒሳቦቹ ከዓመት ወደ ዓመት በሂሳብ መግለጫዎቹ ላይ የሚታዩ ከሆነ ታአማኒነትን ከማሳጣታቸውም በላይ የመንግስትና የሕዝብ ኃብት ለብክነት ስለሚጋለጥ ተቋማቱ በደንብና መመሪያ መሰረት እንዲያወራርዱ እና መሰብሰብ የማይችሉትን ደግሞ አጣርተው እርምጃ እንዲወስዱ አስተያየት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
#ግብርና፡ በ #አማራ_ክልል በተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት እጥረት ምክንያት የመኸር እርሻቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉ የክልሉ አርሶ አደሮች ገለጹ

በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን አነደድ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አቶ ባይነሳኝ እንዳወቀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ምክንያት በቆሎ መዝራት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

የበቆሎ ማሳችንን ሙሉ በሙሉ በሰብል መሸፈን አልቻልንም ያሉት አርሶ አደሩ፤ ይህም የመኸር እርሻቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳንችል ተፅዕኖ ፈጥሮብናል ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩልም ስንዴና ጤፍ መዝራት የሚያስችል የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት በስፋት በገበሬ ቀበሌ ማኅበራት በኩል እየቀረበ አይደለም ብለዋል። የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና በመሆኑ ችግሩ ባስቸኳይ ሊፈታልን ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ በበኩሉ ያለውን ችግር ለመፍታት የሰብል ለውጥ አድርገው እንዲዘሩ እየሠራን ነው ብሏል።
https://press.et/?p=103495
ዜና፡ #በኢትዮጵያ የአትክልት እና ፍራፍሬ አመጋገብ ባህል እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ #የአትክልት እና #ፍራፍሬ አመጋገብ ባህል እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ አንድ ጥናት አመላከተ፤ ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ በተሻለ ደረጃ ተጠቃሚዎች መሆናቸውም ተገልጿል። ይህም በቀላሉ ልንከላከላቸው የምንችለው በሽታዎች ተጋላጭ እንዳደረገን ጥናቱ አስታውቋል።

አትክልክት እና ፍራፍሬ እንዳንመገብ እንቅፋት የሆነብን የዋጋው መወደድ እና ያለን ገቢ አነስተኛ መሆኑ እንደሆነም በጥናቱ ተጠቁሟል። ይሁን እንጂ ይላል ጥናቱ፣ ደህና ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ጭምር የአትክልት እና ፍራፍሬ አጠቃቀም ባህላቸው አናሳ ነው፤ #የአለም የጤና ድርጅት በምክረ ሀሳብነት ካቀረበው መመገብ ያለብን የአትክልት እና ፍራፍሬ መጠን ጋር ሲነጻጸር ባለሃብት ኢትዮጵያውያን የሚመገቡት አነስተኛ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያውያንን የአትክልት እና ፍራፍሬ አመጋገብ ባህል ለማሳደግ እና በከተሞች አቅርቦቱ በበቂ ሁኔታ እንዲኖር ለማስቻል ትልቁን ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ማለትም ነጋዴዎች እና ቸርቻሪዎች መሆናቸውን ጥናቱን ያካሄደው ተቋም CGIAR በምክረ ሀሳብነት አስቀምጧል።

https://rb.gy/ptilk
#ትግራይ ክልል ከ700 በላይ ሰዎች #በረኀብ እንደሞቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ

በትግራይ የምግብ ርዳታ ሥርጭት ማቋረጣቸውን ተከትሎ፣ ከክልሉ ካሉ ሰባት ዞኖች ውስጥ በሶስቱ 728 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን ትግራይ ክልል የአደጋ ዝግጁነት ኮሚሽን መሪ ገብረህይወት ገብረ እግዚአብሔር አሶሺዬትድ ፕሬስ ገልፀዋል፡፡

“በክልሉ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ በርካታ ሰዎች በምግብ እጥረት የተነሳ በመሞት ላይ ናቸው” ሲሉ ገብረህይወት ተናግረዋል፡፡

በረኀብ ከሞቱት ከ728ቱ ውስጥ 350ዎቹ፣ በክልሉ ለሁለት ዓመታት በተካሔደው ጦርነት ምክንያት፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከተጠለሉበት ሰሜን ምዕራባዊ ዞን እንደኾኑ፣ ዘገባው አመልክቷል፡፡ እ.አ.አ መጋቢት አጋማሽ ላይ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የተራድኦ ድርጅት ባለሥልጣናት፣ የዞኑ ትልቋ ከተማ በኾነችው ሽሬ በሚገኝ ገበያ፣ ለ134 ሺሕ ሰዎች የሚበቃ የምግብ ርዳታ ሲሸጥ ማግኘታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡

https://amharic.voanews.com/a/hunger-kills-hundreds-Ethiopia-s-Tigray/7158843.html?fbclid=IwAR1VigT3HdNtFyOxd_dfNMI_2zHa07CKVxDrCMxFO0C7Ut55zzblWXY_1Mg
ዜና፡ በ #ደብረ-ብርሃን መጠለያ ካምፖች ውስጥ ከ116 በላይ ተፈናቃዮች በኩፍኝ በሽታ መያዛቸው ተገለፀ

በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን ከተማ ከ27 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ወይንሸትና ቻይና መጠለያ የመጠለያ ካምፖች የኩፍኝ በሽታ መከሰቱን፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ሃላፊዎችን ዋቢ አድርጎ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎቹ ከፍተኛ የምግብ እጥረት በማጋጠሙና ተፈናቃዮች በሽታውን ለመቋቋም አቅም ስላነሳቸው በሽታው ሊከሰት መቻሉን የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት መምርያ ኃላፊ አቶ አበባው ተናግረዋል፡፡

“አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው ተጠልለው የሚገኙት፤” ያሉት አቶ ደረጀ፣ በዞኑ በሚገኙ 17 የመጠለያ ካምፖች ብቻ ከ90 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉና ሁሉም ተፈናቃዮች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

https://rb.gy/1oq38
ዜና፡ #ይርጋጨፌ ቡና #በቻይና ከሻይ ጋር በመቀላቀል ልዩ ጣዕም ፈጥሯል ተባለ

ይርጋጨፌ ቡና በቻይና #ከሻይ ጋር በመቀላቀል የፈጠረው ጣዕም በቻይናውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማግኘቱን ዢንዋ ባስነበበው ዘገባ አስታውቋል።

የቻይና ህዝብ ሻይ በመጠጣት ባህሉ የሚታወቅ ቢሆንም ቡናም በማጣጣም ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው ዘገባው አዲሱ የቻይና ትውልድ የቡና ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት 2022 በቻይና ገበያ በኦንላይን የተሸጠ የቡና መጠን #27 ነጥብ 6ቢሊየን ዶላር ማውጣቱን ያስታወቀው የዜና አውታሩ ከሶስት አመታት በኋላ #ከ50 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚደርስ መተንበዩን አመላክቷል። ይህም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የቻይናውያን የቡና ፍላጎት ያሳያል ተብሏል።

በቻይና በጥቂት ሰዎች ብቻ ይዘወተር የነበረው ቡና በአሁኑ ወቅት ሰዎች በቡድን ተሰባስበው የሚጠጡት ሁኗል ሲል ካሽ ኮፊ የተሰኘ የቡና ምርት በማቅረብ ላይ የሚገኝ የቻይና ኩባንያ መስራች ያኦ ሲዪ ገልጸውልኛል ሲል ያስነበበው ዢንዋ አዲሱ የቻይና ትውልድ የቡና ማሽኖችን በመግዛት እቤታቸው እንዴት ማፍላት እንደሚችሉ ትምህርት በመከታተል ላይ እንደሚገኙም ነግረውኛል ብሏል።
https://rb.gy/v54e6
ዜና፡ #በትግራይ የምግብ እርዳታ በመቋረጡ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች መጨመሩ #አሜሪካ ድጋጤ ፈጥሮብኛል ስትል ገለጸች

በኢትዮጵያ የረድኤት ድርጅቶች የምግብ እርዳታ አቅርቦታቸውን በማቋረጣቸው ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተዘግቧል። አሶሼትድ ፕሬስ በትግራይ የሚገኙ ባለስልጣናት በክልሉ በሚገኙ ሰባት ዞኖች የምግብ እርዳታ ከተቋረጠ ወዲህ #728 ሰዎች መሞታቸውን ገልጸውልኛል ሲል ዘግቧል።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ለዜና አውታሩ በላከው የኢሜይል መልዕክት በእርዳታው መቋረጥ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች መጨመሩ ድንጋጤ እንደፈጠረበት አስታውቋል።
እርዳታ ስርጭቱን የማቆም ውሳኔ እጅግ መራራ መሆኑን

የገለጸው ተራድኦ ድርጅቱ በየትኛውም ሀገር ተፈጽሟል ተብሎ የማይገመት መጠን ያለው የምግብ እርዳታ በኢትዮጵያ መሰረቁን አመላክቷል።
በምግብ እጦት ከሚሰቃይ ህዝብ ጉሮሮ ስርቆት መፈጸም ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር ነገሩ ከአይምሮ በላይ ነው ሲል በአጽንኦት ኮንኗል።
https://rb.gy/q8djx
#ኢትዮጵያ: ከ86 ሺ በላይ ሀሰተኛ የአሜሪካን ዶላር ለመመንዘር ይዞ የተገኘው ግለሰብ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ 86ሺ 600 ሀሰተኛ የአሜሪካን ዶላር እንደ እውነተኛ አስመስሎ ሊመነዝር ሲል እጅ ከፍንጅ በተያዘው ታደሰ ኃ/ማርያም ላይ ክስ መስርቶበት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አድርጓል በማለት የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሹ ለጊዜው ካልተያዘው ግለሰብ ጋር በመሆን ህዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ዲአፍሪክ ሆቴል ተብሎ ከሚታወቀው አካባቢ ኦዚ ካፌ ውስጥ 86ሺ 600 ሀሰተኛ የአሜሪካን ዶላር እንደ እውነተኛ አስመስሎ በመመንዘር እንዲዘዋወሩ ለማድረግ ሲል እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ ሀሰተኛ ገንዘብ ይዞ መገኘት ወንጀል በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 359 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ክስ የቀረበበት ሲሆን እንዲሁም በዚሁ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ፖሊስ መምሪያ ተጠርጥሮ በህግ አግባብ ተይዞ ታስሮ ካለበት የማቆያ ቤቱን በር በመገንጠል ከእስር ቤቱ ያመለጠ በመሆኑ ከእስር ማምለጥ ወንጀል የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 461/2/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ሁለት ተደራራቢ ክሶች ቀርበውበታል። https://www.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid0e8FjgUHxbVRMnPpWznaVpiDZUxncJXpbSSjxUDoc5UNhDNgcvBcSeHT3BzTvcWeKl
ዜና፡ የአርቲስት #ሀጫሉ_ሁንዴሳ ገዳዮች ማንነት እውነት እንዲወጣ ባለቤቱ ፋንቱ ደሚሴ ጠየቀች

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ገዳዮች ማንነት እውነት እንዲወጣ ባለቤቱ ፋንቱ ደሚሴ ትላንት ሰኔ 22 ቀን በተካሄደው ሁለተኛው የሀጫሉ ሁንዴሳ አዋርድ መርሃ-ግብር ላይ በደረገችው ንግግር ጠየቀች፡፡

የአርቲስቱ ባለቤትና የሀጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን ሰብሳቢ ፋንቱ ሶስት አመት ሙሉ የሀጫሉን ግድያ ፍትህ አላየሁም፣ እውነቱ እስካልወጣ ድረስ ለእኔ ማንም ንፁህ አይደለም ስትል ገልፃለት፡፡

ለአሸናፊ አርቲስቶችና የኪነጥበቡ ባለሙያዎች ሽልማትና እውቅና በተሰጠበት መርሃ-ግብር ባደረገችው ንግግር ፣ “ ጥለሀን ከሄድክ በኋላ እውነት ላይ ተኝተው እኛ እንዳለን አለን፣ የበላህም፣ ያስበላህም ዘመድ ይሁን ጠላት ሳናውቅ አለን፣ የሀገራችን ነገር አለባብሶ ማለፍ ነው” ስትል ተናግራለች፡፡
https://rb.gy/k21hu
ዜና፡ የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ ሀይሎች በዘፈቀደ #በአደባባይ የሚፈጸሙ ግድያዎች እየጨመሩ መጥተዋል፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ አለመሆን አሳሳቢ ሁኗል

የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በክልሎች አሰቃቂ ግድያ ሲፈጽሙ የሚያሳይ በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በስፋት ተሰራጭተዋል። ባለፈው አመት ሰዎች በህይወት እያሉ ሲቃጠሉ የሚያሳይ ምስል በስፋት ተሰራጭቷል። ይህ አሰቃቂ ድርጊቱ ከተፈጸመ 15 ወራትን ቢያስቆጥርም #የፌደራል መንግስቱም ይሁን #የክልሉ መንግስት ድርጊቱን ፈጻሚዎች በግልጽ ክስ አልመሰረቱባቸውም። በወቅቱ ከድርጊቱ ጋር በተገናኘ የተጠረጠሩ አራት ሰዎች በቁጥጥር ስር ቢውሉም ክስ ይመስረትባቸው ወይም ፍርድ ይሰጣቸው የሚታወቅ ነገር የለም።

በኦሮምያ ክልል በአደባባይ የተገደለው አማኑኤል ወንድሙን ጨምሮ በርከታ የሀገሪቱ ሰዎች ከፍርድ ሂደት ውጭ የጸጥታ ሀይል መለዮ በለበሱ የመንግስት ሀይሎች ተንቀሳቃሽ ምስል በማስደገፍ በግልጽ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። #በጋመቤላ በጸጥታ ሀይሎች የተፈጸመው ጭፍጨፋ 50 ሰዎችን ቀጥፏል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮሚሽነር #አብዲ ጂቢር (ዶ/ር) ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ኮሚሽኑ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተፈጸሙ እና በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፉ ወንጀሎች ዙሪያ መረጃዎች አሰባስቧል። ኮሚሽኑ ባካሄደው ምርመራ ያገኘውን ውጤት እና ምክረ ሀሳብ ለመንግስት ማቅረቡንም አስታውቀዋል።

https://rb.gy/cr74k
ዜና ትንታኔ፡ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤትና ፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጨምሮ በስምነት የፌዴራል እና የክልል መንግስት ተቋማት ላይ ክስ አቀረቡ

በብሩክ አለሙ

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ከታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ የዎላይታ ብሄር የራሱን እድል በራሱ የመወሰንና ራሱን የማስተዳደር መብትን በመጠቀም በክልል የመዳራጀት ህግን በመከተል ያቀረበዉን የመብት ጥያቄ ተከትሎ በብሔሩ ግለሰብ አባላትና በቡድን እንዲሁም በብሔሩ ላይ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፈፅመዋል ባሏቸው አካላት ላይ ክስ አቀረቡ፡፡

ፓርቲዎቹ ክሱን ያቀረቡት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት( 1ኛ ተከሳሽ) ፣በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት( ጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት) (2ኛ ተከሳሽ)፣ በኢትዮዽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ( 3ኛ ተከሳሽ)፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መንግስት(የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት) (4ኛ ተከሳሽ) ፣በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ምክር ቤት( 5ኛ ተከሳሽ) ፣ በወላይታ ዞን አስተዳደር(6ኛ ተከሳሽ)፣በወላይታ ዞን ምክር ቤት(7ኛ ተከሳሽ) እና ብልጽግና ፓርቲ ( 8ኛ ተከሳሽ) ላይ ሲሆን ክሱን የመሰረቱት ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ነው፡፡

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና ስራ አስፈፃሚ አባልና የወላይታ ወጣቶች አደረጃጀት አመራር የሆኑት አቶ አሸናፊ ከበደ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ለተከሳሶቹ መጥሪያው እንደደረሳቸው ገልፀው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የመሰረታዊ መብቶችና ነጻነት ችሎት ፍ/ብሄር ምድብ ክስ ችሎት ለሀምሌ 3 የፅሁፍ መልስ እንዲሰጡና ለሀምሌ 7 ደግሞ ለቃል ክርክር ቀጠሮ ሰጥቷል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

https://rb.gy/lh492
አንድን ግለሰብ በመግደል አስከሬኑን ቆራርጠው መጸዳጃ ቤት ውስጥ የጣሉት ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ

678 ሺህ ብር የሚያወጣ በዱቤ የተሸጠን በቆሎ ለግል ጥቅማቸው ለማዋል የንብረቱን ባለቤት በመግደል አስከሬኑን በመቆራረጥ መጸዳጃ ቤት ውስጥ የጣሉት ሁለት ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው በሀዲያ ዞን ዱና ወረዳ መሆኑን የደቡብ ክልል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከተከሳሾቹ አንዱ የንብረቱን ባለቤት በጥይት ከገደለ በኋላ አስከሬኑን ሁለቱም ተከሳሾች ቆራርጠው በማዳበሪያ በመጠቅለል መጸዳጃ ቤት ውስጥ መክተታቸው ተገልጿል፡፡

የወረዳው ፖሊስም ለአራት ቀናት ያህል ባደረገው ፍለጋ÷ አገልግሎት መሥጠት ባቆመ አሮጌ መጸዳጃ ቤት ውስጥ የሟችን የተቆራረጠ አስከሬን ማግኘቱን አስታውቋል።

ወንጀሉን የፈጸሙት በድለላ ሥራ የሚተዳደርና በሟች ግቢ ውስጥ ቤት ተከራይቶ የሚኖር አቶ ፈለቀ በቀለና በጫኝና አውራጅ የቀን ሥራ የሚተዳደር አቶ ሳሙኤል አበራ የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ አቶ ፈለቀ በቀለ ከግል ተበዳይ አቶ አባተ ኢቶሬ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ግምቱ 678 ሺህ ብር የሆነ 230 ኩንታል በቆሎ ተቀብሎ በዱቤ ማሻሻጡም ነው የተገለጸው፡፡

ይህንኑ ገንዘብ ለግል ጥቅሙ ለማዋል በማሰብም በመጠጥ ተገፋፍቶ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 4 ሠዓት እስከ 8 ሠዓት ባለው ጊዜ የግል ተበዳይን ወደ ቤቱ በመጥራት በጥይት መግደሉ ተረጋግጧል፡፡

ከ2ኛ ተከሳሽ አቶ ሳሙኤል አበራ ጋር በመሆንም የሟችን አስከሬን ቆራርጠው በሦስት ማዳበሪያ በማድረግ መጸዳጃ ቤት ውስጥ መክተታቸውን 1ኛ ተከሳሽ አረጋግጧል፡፡

የሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሁለቱም ተከሳሾ በሞት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

ፋና
በዲማ ወረዳ ለግዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ የሁለት የአካባቢ ሚሊሻዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ገለፀ።

በጋምቤላ ክልል በአኙዋ ብሔረሰብ ዞን በዲማ ወረዳ ለግዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ የሁለት የአካባቢ ሚሊሻዎች ሕይወት ሲያልፍ አንድ ሚሊሻ መቁሰሉን የዲማ ወረዳ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ኡኬሎ ኡጁሉ ገልፀዋል።

እንደ ሃላፊው ገለፃ ሰኔ 24 ዕለት ከጥዋቱ 2 :00 ላይ ለግዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በካችና ቀበሌ አካባቢ ገብተው በከፈቱት ተኩስ በሰዓቱ ፀጥታ በማስከበር ላይ የነበሩ ሁለት የአካባቢ ሚሊሻዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ አንድ ሚሊሻ ደሞ ቆስሎ በህክምና ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ኡኬሎ አያይዘውም ሰኔ 23 ዕለትም ከቀኑ 3:00 አካባቢ ከካችና ቀበሌ ወደ ናምካዶ ቀበሌ በመጓዝ ላይ የነበረው አንድ ሞተረኛ በጥይት ተመትቶ ጉዳት እንደደረሰ ገልፀዋል።

ሃላፊው አክለውም በወረዳው ላይ የተሻለ ሰላም ቢኖርም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በመንገድ ላይ ዝርፊያ የተሠማሩ ሽፍቶች በተደጋጋሚ ጥቃት እየፈፀሙ መሆኑን ገልፀው የወረዳው መንግስት ጥቃቱን ለማስቆም ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት የአቅሙን ያህል እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።


ምንጭ- ዲማ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
እለታዊ ዜና፡ የ #አማራ_ክልል የገጠመው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ለዘመናት የተሰበከው የልዩነት ሃሳብ ውጤት መሆኑን አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለፁ

የአማራ ክልል የገጠመው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለዘመናት የተሰበከው የልዩነት ሃሳብ ውጤት በመሆኑ ችግሮችን ገምግሞ እና አርሞ መውጫ በሮችን ማዘጋጀት ተገቢ ነው ሲሉ የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለፁ፡፡

ኃላፊው ለክልሉ አሁንም ድረስ አጀንዳዎችን በመወርወር አካባቢውን ሠላም የራቀው ቀጣና ለማድረግ የሚሰሩ መኖራቸውን ጠቅሰው የተለያየ ፍላጎት ያላቸው እና በውስጥም በውጭም ያሉ ኃይሎች የክልሉን ሠላም ለማወክ ቀን ከለሊት እየሰሩ ነው ብለዋል።
https://rb.gy/7vdjh
ዜና ትንታኔ፡ በኮንደሚኒየም ቤቶች ላይ የወጣው አዲስ የግብር ተመን የህዝቡን አቅም ያላገናዘበ፣ የህግ ክፍተት ያለበት እና ማህበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የህግ ሙሁራንና የቤት ባለንብረቶች ገለጹ

በሞላ ምትኩ

በአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎቸ ቢሮ የተላለፈውና በትግበራ ላይ ያልው የቤት ጣራና ግድግዳ ግብር አዲስ የክፊያ ተመን በአሁኑ ወቅት ያለውን ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ እና አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት በህዝቡ ላይ የፈጠረውን አሉታዊ ጫና በከፋ ደረጃ የሚያባብስ ከመሆኑም በላይ የህግ ክፍተት እንዳለበት በጋራ መኖሪያ ህንጻዎች የቤቶች ባለንብረቶች እና የህግ ሙሁራን ተናገሩ።

በአቃቂ ቃሊቲ ከፍለ ከተማ በቂሊንጦ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለንብረቶች ለአዲስ ስታንዳርድ አንደገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ህዝቡ በአስጭናቂ የኑሮ ሁኔታ ላይ እንዳለ እያወቀ አንዳንድ ማስተካከያዎች ቀድመን አንዳናደርግ አስቀድሞ ሳያሳውቀን ድንገተኛ የግብር ክፍያ አስገዳጅ ማምጣቱ አግባብነት የለውም ይላሉ።

https://rb.gy/e4wm0
ዜና፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ ሁለት የፖሊስ አዛዦች በጥይት ተገደሉ

በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለ እና የወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ም/ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ ወርቁ ሽመልስ ትላንት ሰኔ 26፣ 2015 ለስራ በወጡበት ለጊዜው ማንነቱ ባልታወቀ አካል በተከፈተባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አስታወቀ፡፡

የፖሊስ አዛዦቹ ላይ ጥቃቱ የተከፈተባቸው ትላንት ከቀኑ 8፡ዐዐ ሰዓት አካባቢ በደጀን ወረዳ ኩራር ቀበሌ ደምበዛ ጎጥ የሚሰጠውን የ8ኛ ክልላዊ ፈተና የጸጥታ ስራ ለመከታተል በወጡበት መሆኑን የወረዳው አስተዳደር ገልጧል፡፡ አብሯቸው መኪና በማሽከርከር ላይ የነበረ አንድ የፖሊስ አባል ቆስሎ ህክምና እየተደርገለት እነደሚገኝ ገልጧል፡፡
https://rb.gy/v8em2
የፀጥታ ኃይል ልብስ በለበሱ ሰዎች ታግቼ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት ተዘርፍኩ ያለው አሽከርካሪ ንብረቱን ሸጦ የሀሰት ክስ መመስረቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

አሽከርካሪው ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ/ም የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-35747 ኢ/ት በሆነ ተሽከርካሪ አዳማ ከሚገኝ ድርጅት ግምቱ 2 ሚሊዬን 7መቶ ሰላሳ ሺ 240 ብር የሚያወጣ የፌሮ ብረት መርካቶ ከሚገኝ የግል ተበዳይ ሱቅ ለማራገፍ ይጭናል።

የፀጥታ ኃይል ልብስ የለበሱ አካላት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ አግተው ንበረቱን እንደዘረፉት በአቃቂ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለቃሊቲ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ያመለክታል፡፡

ፖሊስ ጣቢያው ለጉዳዩ ልዮ ትኩረት በመስጠት ወንጀል ፈፃሚዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ንብረቱን ለማስመለስ ባደረገው በርቱ ክትትልና ባሰባሰበው መረጃ አሽከርካሪው ብረቱን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 አካባቢ ሸጦ ተሽከርካሪውን ጀሞ አካባቢ ማቆሙን ይደርስበታል፡፡

በግለሰቡ ላይ ምርመራው ቀጥሎ ከተሰረቀው ንብረት መካከል ግምቱ 648ሺ 432 ብር የሚያወጣ ብረት ማስመለሱን ፖሊስ ጣቢያው አስታውቋል። የተጣለበትን እምነት ወደኋላ በማለት ንብረቱን ሸጦ ሳይታገት ታግቻለሁ በማለት ፖሊስን ለማሳሳት ሀሰተኛ ክስ የመሰረተው አሽከርካሪ እና የተሰረቀውን ንብረት የገዛውን ጨምሮ በአጠቃላይ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን መቀጠሉን ፖሊስ አስታውቋል።

አንዳንድ ግለሰቦች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማቀድ ሳይታገቱ ታግተናል በማለት ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጬ እና ሳይዘረፋ ተዘርፈናል በማለት የግል ጥቅማቸውን በህገወጥ መንገድ ለሟሟላት የሚሯሯጡ መኖራቸውን ያስታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ የተለያዩ ሚዲያዎች የእነዚህ ህገወጦች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ መልእክቱን አስተላልፏል ።