Event Addis Media – Telegram
Event Addis Media
9.61K subscribers
6.13K photos
14 videos
4 files
4.75K links
Connect with Addis artistic community!

Website: https://eventaddis.com

Contact: @Tmanaye
Download Telegram
"እየዳነ ሄደ" መጽሐፍ አርብ ይመረቃል

የደራሲና ገጣሚ ምግባር ሲራጅ "እየዳነ ሄደ" መጽሐፍ የፊታችን አርብ ግንቦት 23 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:30 ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጻሕፍት ውስጥ ይመረቃል።

በምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይ ልዩ ልዩ ተጋባዥ እንግዶች የሥነጽሑፍ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።

ከሰሞኑ ለንባብ የበቃው የገጣሚና ደራሲ ምግባር ሲራጅ "እየዳነ ሄደ" መጽሐፍ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ ሲሆን በ280 ገፆች ተቀንብቦ በ450 ብር  የጀርባ ዋጋ ለአንባቢያን ቀርቧል።

ገጣሚና ደራሲ ምግባር ሲራጅ ከዚህ ቀደም "ዘንባባ" እና "መንደሪን መንደሪን" የተሰኙ መጻሕፍትን ለአንባቢያን ማቅረቡ ይታወሳል።

ለተጨማሪው: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
በአርቲስት ሒሩት በቀለ ስም የስኳር ሕመምተኞች ፋውንዴሽን ሊቋቋም ነው

በአርቲስት ሒሩት በቀለ ስም የስኳር ሕመምተኞች ፋውንዴሽን ሊቋቋም መሆኑ ተነገረ።

የአርቲስቷን የግል የሕይወት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ታትሞ በግንቦት 19 2016 ዓ.ም ለገበያ የቀረበ ሲሆን፥ የመጽሐፉ የሽያጭ ገንዘብ ለስኳር ሕሙማን ወገኖች መርጃ ይውላል ነው የተባለው።

በመርሐግብሩ ላይ የአርቲስቷ ወዳጅ ዘመዶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተዋል።

የሂሩት በቀለን የጥበብ ስራዎች፣ በፌደራል ፖሊስ የማርቺንግ ባንድ ኦርኬስትራና በዳዊት ፅጌ ባንድ በሚታጀቡ ድምፃውያን በልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ ክንውኖች እየተዘከረ ይገኛል።

አርቲስት ሂሩት በስኳር ህመም ምክንያት ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው።

መረጃው የአራዳ ኤፍ ኤም 95.1 ነው።

ለተጨማሪ: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
"ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ" ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን የፊታችን ሐሙስ ይከፈታል

ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን "ኢትዮጵያን እንገንባት" (ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ) በሚል መሪ ሀሳብ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ከግንቦት 22 እስከ 24 በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።

በኤግዚቢሽኑ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ከ156 የአገር ውስጥና የውጪ አገር ድርጅቶች እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን ከ5 ሺህ በላይ ጎብኚዎች በኦንላይን ተመዝግበዋል ተብሏል ።

በባለፈው ዓመት ተመሳሳይ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን የተካሄደ ሲሆን የዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና እና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በጋራ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

ለተጨማሪ: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
አዲስ አድማስ ጋዜጣ ይቅርታ ጠየቀ

ባሳለፍነው ቅዳሜ ለአንባቢያን የደረሰው የአድማስ አድማስ ጋዜጣ የሌላ ጋዜጣ( የአዲስ ልሳን ጋዜጣን)  ገፆችን ይዞ መውጣቱ በጋዜጣ አንባቢያን ዘንድ ውዥንብር እንደፈጠር ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ተመልክቷል።

የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍሉም ስለተፈጠረው ጉዳይ ማብራሪያ ከሰጠ በኃላ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

የአድማስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መልዕክት የሚከተለውን ይመስላል

"ለውድ አንባቢያን፡-ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ ከዚህ ቀደም ያላጋጠመ ትልቅ ስህተት ተፈጥሯል፡፡ በብርሃንና ሰላም ማተምያ ቤት በተከሰተ “የቴክኒክ ችግር” ሳቢያ፣  የሌላ  ጋዜጣ ገጾች ተቀላቅለው (ከእኛ ዕውቅና ውጭ) ለሥርጭት በቅቷል፡፡

ጋዜጣው ለሥርጭት ከመብቃቱ በፊት ስህተቱን ብናውቅ ኖሮ፣ ከሥርጭት ማገድ እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን እኛም መረጃው የደረሰን ከውድ አንባቢያን በመሆኑ ከማዘንና ይቅርታ ከመጠየቅ ውጭ ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ ከማተምያ ቤቱ ጋር በነበረን የ25 ዓመት ገደማ የጠበቀ የሥራ ግንኙነት፣ በየጊዜው ትናንሽ ስህተቶች ቢፈጠሩም፣ የአሁኑን ያህል ከባድ ስህተት አጋጥሞን አያውቅም፡፡

ከማተምያ ቤቱ ማናጅመንት ጋር በመነጋገር ስህተቱ የተፈጠረበትን ትክክለኛ  ምክንያት ለማወቅና ዳግም መሰል ስህተቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ እየጣርን ነው፡፡ የራሳችንንም መፍትሄዎች እናበጃለን፡፡

ለአሁኑ  ስህተት ግን ውድ የጋዜጣውን አንባቢያን በድጋሚ ከልባችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ የጋዜጣችንን የጥራት ደረጃ የማሳደግና ተነባቢ የማድረግ ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡"

ለተጨማሪው: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
"ለተሻለ ነገ እናንብብ" አውደርዕይ ዛሬ ይከፈታል

በኢትዮጵያ የኤፍ ኤም ሬድዮ ታሪክ ቀዳሚው የሆነው የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የ24ኛው ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀው "ለተሻለ ነገ እናንብብ " የተሰኘ የመጻሕፍት አውደርዕይ ከዛሬ ግንቦት 21 እስከ 27 2016 ዓ.ም ሸጎሌ በሚገኘው በአዲሱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሚዲያ ኮምፕሌክስ ግቢ ውስጥ ይካሄዳል።

በርካታ የመጻሕፍት አቅራቢዎች ቅናሽ የተደረገባቸውን መጻሕፍት በአውደርዕዩ ላይ ይዘው ይገኙበታል።

በየዕለቱ አንባቢያን ከሚያደናቋቸው ደራሲያን ጋር የሚገናኙበት ዝግጅቶችም ተሰናድተዋል።

መግቢያው በነፃ ስለሆነ ማንኛውም የመጻሕፍት ወዳጅ እዚህ የመጻሕፍት አውደርዕይ ላይ መሳተፍ ይችላል ተብሏል።

ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላለፉት ወራት "ለተሻለ ነገ እናንብብ" የተሰኘ የ100 ቀናት የንባብ ዘመቻ ሲካሄድ እንደቆየ ይታወሳል።

ለተጨማሪው: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
ውድነህ ክፍሌ የክብር የእንግዳ የሆነበት አንጋፋው የኪነጥበብ ምሽት ዛሬ ይካሄዳል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል የሚዘጋጀው የኪነጥበብ መርሃግብር ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 21 2016 ዓ.ም ይካሄዳል።

በዕለቱ ፀሐፊ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ "የአንድ ግጥም፣ የአንድ ወግ" የክብር እንግዳ ሆኖ  ይገኛል።

እንዲሁም ግጥሞች፣ ወግ፣ ሙዚቃና ሞኖሎግ ተሰናድተው እናንተ ውድ ታዳሚዎቻችንን በባህል ማዕከል አዳራሽ ከቀኑ በ11: 30 ጀምሮ ይጠብቃችኃል ብለዋል አዘጋጆቹ ።

ማስታወሻ :— ፕሮግራሙ ላይ ለመታደም የምትፈልጉ በአሁን ሰዓት የዩኒቨርስቲው ተማሪ ያልሆናችሁ የስነ ጽሑፍ አፍቃሪያን መግቢያው በ5ተኛ በር በኩል ነው።

ለተጨማሪው: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
የአንጋፋ ሠዓሊያን ስራዎች የሚቀርብበት "የኢትዮጵያ ቀለም 3"የሥዕል አውድርዕይ ዛሬ ይከፈታል

የስምንት አንጋፋ ሠዓሊያን የሥዕል ስራዎች የሚቀርብበት "የኢትዮጵያ ቀለም 3" የሥዕል አውደርዕይ ዛሬ ግንቦት 21 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ በፈንድቃ ባህል ማዕከል ውስጥ ለእይታ ይበቃል።

በዚህ የሥዕል አውደርዕይ ላይ ስራዎቻቸው የሚቀረብላችው ሠዓሊያን ወርቁ ጎሹ ፣ ባርባራ ጎሹ ፣ገብረክርስቶስ ሰለሞን ፤ዘሪሁን የትምጌታ ፤አሸናፊ ወለደየሱስ ፣ አይናለም ገ/ማርያም ፣ አክሊሉ መንግስቱ ናቸው።

የሥዕል አውድርዕዩ ከግንቦት 21 እስከ ሰኔ 5 2016 ዓ.ም ድረስ በፈንድቃ በእይታ ላይ ይቆያል ተብሏል።

ለተጨማሪው: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
ደራሲ ሔኖክ በቀለ "ሀገር ያጣ ሞት" ከተሰኘው መጽሐፌ ላይ በቤተልሔም ታፈስ ያለፍቃዴ ጽሑፍ ተወስዶብኛል ሲል ቅሬታውን አቀረበ

ደራሲ ሔኖክ በቀለ "ሀገር ያጣ ሞት" የተሰኘውን የመጀመሪያ መጽሐፉን በ2013 ዓ.ም ነው ለንባብ ያበቃው። በቀድሞ "ኤልቲቪ ሾው" አቅራቢነት የምናውቃት ቤተልሔም ታፈስ ደግሞ ከወራት በፊት "5 ጉዳይ" የተሰኘ መጽሐፏን ለንባብ አብቅታለች።

ደራሲ ሔኖክ በቀለ እንደሚለው ከሆነ "ከሀገር ያጣ ሞት መጽሐፌ ገጽ “132” ላይ ያለው አንቀጽ አንዲትም ቃል ሳይቀየር የአንቺ “5 ጉዳይ” በተሰኘ መጽሐፍ ገጽ 164 ላይ ተጽፏል" ሲል ደራሲው ተናግሯል።

ጸሐፊዋ ይህንን ስታደርግ ምንም አይነት የሌላ መጽሐፍ ሀሳብ መሆኑን አመላካች የሆነ ነገር ያልተጠቀመች እንደሆነ ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ተመልክቷል ደራሲውም "መጠቀም ከፈለግሽም በቀላሉ በትምህርተ ጥቅስ አድርገሽ ምንጭ ጠቅሰሽ መጠቀም ትችይ ነበር። ይሄ የአዋቂ ተግባር እንጂ መዋረድ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ነገር የሥራሽንም የሰብዕናሽንም ንጽሕና ያጎድፋል።" ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።

ደራሲው"ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፉ ከተጻፈለት አጀንዳ ውጪ ለፖለቲካዊ ዲስኮርስ ጠምዝዞ መጠቀም የፈጠራ ሥራን ጠንቅቆ ያለመረዳት የዋኀነትና ድፍረት ነው። ..ሥራችንን አክብረንና ወደን ዋጋ እንከፍልበታለን። ለጥራቱና ለውበቱ በገንዘብ የማይታመን ዋጋ እናወጣለን። ማንም እንዳሻው ዘግኖና ከታትፎ ሊጠቀመው አይገባም። "ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

ኤቨንት አዲስ ድረገፅ የ"5 ጉዳይ" ጽሐፊ ቤተልሔም ታፈሰ በዚህ ጉዳይ ምላሽ እንድትሰጠን ያደረገው ሙከራ ያልተሳካ ሲሆን  ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ በሆነች ጊዜ ሀሳቧን ለማስተናገድ በራችን ክፍት እንደሆነ ለማሳወቅ እንወዳለን።

📍ከላይ የተያያዘውን ፎቶ ይመለከቱ

ለተጨማሪው: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
ጋዜጠኛ መሠለ ገ/ህይወት ከዜናው ዓለም ወደ መዝናኛው ዓለም ሊሸጋገር ነው።

በዜና አንባቢነት የሚታወቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ መሠለ ገ/ህይወት በመዝናኛው ዘርፍ ሊመጣ ነው።

ላለፉት 18 ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዜና አንባቢነት ሲያገለግል የቆየው መሠለ በቅርቡ "መሴ ሾዉ" የተሠኘ የምሽት መዝናኛ ፕሮግራም በአባይ ቲቪ እንደሚጀምር ታውቋል።

መሴ ሾዉ የተሠኘው የምሽት የመዝናኛ ፕሮግራም (late night show) የሠርጌለታ፣ የሙዚቀኞች ብፌ፣ የእንግዳ ቆይታ እንዲሁም እግሬ ሲደርስ የተሰኙ አዝናኝ መሠናዶዎች የተካተቱበት ነው።

ፕሮግራሙ በየሣምንቱ ቅዳሜ ምሽት በአባይ ቲቪ ከመተላለፉ ባሻገር መሴ ሾው በሚል ስያሜ በተከፈተ በራሱ የዩቲዩብ ቻናል ለተመልካች የሚደርስ ይሆናል።

ጋዜጠኛ መሠለ ከሁለት ዓመታት በፊት የመልካሙ ተበጀንና የንዋይ ደበበን ዘፈኖች በመጫወት የመዝናኛ ተሥጥዖውን ማሣየቱና ተመልካቾችን ማሥደመሙ ይታወሳል።

መረጃው የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ነው።

ለተጨማሪው: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1
Event Addis Media
ደራሲ ሔኖክ በቀለ "ሀገር ያጣ ሞት" ከተሰኘው መጽሐፌ ላይ በቤተልሔም ታፈስ ያለፍቃዴ ጽሑፍ ተወስዶብኛል ሲል ቅሬታውን አቀረበ ደራሲ ሔኖክ በቀለ "ሀገር ያጣ ሞት" የተሰኘውን የመጀመሪያ መጽሐፉን በ2013 ዓ.ም ነው ለንባብ ያበቃው። በቀድሞ "ኤልቲቪ ሾው" አቅራቢነት የምናውቃት ቤተልሔም ታፈስ ደግሞ ከወራት በፊት "5 ጉዳይ" የተሰኘ መጽሐፏን ለንባብ አብቅታለች። ደራሲ ሔኖክ በቀለ እንደሚለው ከሆነ…
የቤተልሔም ታፈሰ ምላሽ እና ይቅርታ

ደራሲ ሔኖክ በቀለ "ሀገር ያጣ ሞት" ከተሰኘው መጽሐፌ ላይ በቤተልሔም ታፈሰ ያለፍቃዴ ጽሑፍ ተወስዶብኛል ሲል ላቀረበው ቅሬታ የ"5 ጉዳይ" መጽሐፍ ጻፊ ቤተልሔም ታፈሰ ምላሽ እና ይቅርታ ለደራሲው እንዳቀረበች ኤቨንት አዲስ ድረገጽ ተመልክቷል።

የ"5 ጉዳይ" መጽሐፍ ጻፊ ቤተልሔም ታፈሰ የሰጠችው ምላሽ እና ይቅርታ እንደሚከተለው ይቀርባል።

"ታላቅ ይቅርታ "5 ጉዳይ" በተሰኘው መፅሀፌ ላይ ሰፊ ሽፋን ያገኘው "የባሮ ቱምሳ ገዳይ ማነው?" የሚለው ክፍል ብዙ የደበዘዙ እና የተሸፈኑ ታሪኮችን የገለጠ እና የእውነት ክር ብትቀጥንም እንደማትበጠስ ያሳየ በብዙ ልፋት እና ድካም የተዘጋጀ ስራ  ነው::

ሆኖም ግን ይህ በታሪክ የምርምር ሰነድነት ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል ፅሁፍ፤ ስነፅሁፋዊ ለዛ እንዲኖረው በማሰብ የመግቢያ ክፍል ሲሰናዳለት የመፅሀፌ አርታዒ አንድ አንቀፅ ቃል በቃል እና እንደወረደ ከደራሲ  ሄኖክ በቀለ "ሀገር ያጣ ሞት" የተሰኘ መፅሀፍ ስረአተ ነጥብም ሆነ የህዳግ ማስታወሻ ሳይጠቀም እንዳለ ገልብጦ ተጠቅሟል::

ይህ  ተግባር መፈፀሙን ያወቅሁት ዛሬ ማለዳ የወንድም ሄኖክን ቅሬታ ካነበብኩ በኃላ ነው:: በተፈፀመው ጉዳይ በተለይም ደግሞ እንደ አንድ ፀሀፊ ይህ ጉዳይ ምን ያህል አስከፊ መሆኑን ስለምረዳ ምንም እንኳን በስልክ ከሄኖክ ጋር ስለተፈጠረው ስህተት አስረድቼው የተግባባን ቢሆንም፤ ደራሲ ሄኖክን በአደባባይ ይቅርታ ማለት እፈልጋለሁ:: ከይቅርታ ባለፈም በቀጣይ ህትመት ላይ አንቀፁ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ተቀምጦ በህዳግ ምንጩ ተጠቅሶ እንዲወጣ ለማድረግ ቃል እገባለሁ::

በድጋሚ ለተፈጠረው ስህተት በሙሉ ሀላፊነቱን ወስጄ አንባቢዎቼን በሙሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ::"

@EventAddis1
የሐሙሰ መረጃዎች ደርሰዋል !

የሳምንቱ የመዝናኛ መረጃዎችን በአጫጭሩ እነሆ:

ተከታዩን ሊንክ
https://shorturl.at/uZpnU በመነካት ብቻ የቻናሉን ስፔሻል የሐሙስ መረጃዎችን በድረገጻችን በጥሩ አቀራረብ ማንበብ ትችላላችሁ።

ማሳሰቢያ: የኤቨንት አዲስ ድረገጽ መረጃዎችን በእርሰዎ ሚዲያ ሲጠቀሙ እባክዎ በተገቢው መንገድ ምንጭ ይጠቀሱ።

የEventAddis/ሁነት አዲስ ማኅበራዊ ገፆቻችን:

Telegram:https://news.1rj.ru/str/EventAddis1

Website: https://eventaddis.com

Facebook:https://facebook.com/groups/2009372275938661/

Facebook Page:https://www.facebook.com/profile.php?id=100083170462851&mibextid=ZbWKwL
የሳምንቱ የመጻሕፍት መረጃዎች (በአጭሩ )

📍መጽሐፍ

- የደራሲና ገጣሚ ምግባር ሲራጅ "እየዳነ ሄደ" መጽሐፍ ነገ አርብ ግንቦት 23 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:30 ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጻሕፍት ውስጥ ይመረቃል።በምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይ ልዩ ልዩ ተጋባዥ እንግዶች የሥነጽሑፍ  ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።

-በዶ/ር ወሰን መኮንን የተዘጋጀው "ዚድራር" መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 24 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ጀምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በብሔራዊ ቴአትር ይመረቃል።

- በጋዜጠኛ ዮሴፍ ዳሪዮስ የተተረጎመው "ባይተዋሩ ልዑል" የተሰኘው መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 24 2016 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ጀምሮ በብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት አግልግሎት (ወመዘክር ) አዳራሽ ውስጥ ይመረቃል።በዕለቱም ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ፣ገጣሚ ሀብታሙ ማሞ ፣ ጋዜጠኛ ኃይለየሱስ መኮንን ጨምሮ ሌሎችም ባለሞያዎች ሀሳቦቻቸውን በመድረኩ ያጋራሉ ተብሏል።

-በናትናኤል ከበደ የተዘጋጀው "ዱባይ እንደምን ሰለጠነች?" የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 24 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በኢሊሊ ሆቴል ውስጥ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል።

-የጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ "ዜሮ የስራ ልምድና ሌሎችም ወጎች" የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 26 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 11:ዐዐ ጀምሮ በግዮን ግሩቭ ጋርድን ውስጥ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል።

-የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የ24ኛው ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀው "ለተሻለ ነገ እናንብብ"የተሰኘ የመጻሕፍት አውደርዕይ ከግንቦት 22 እስከ 27 2016 ዓ.ም ሸጎሌ በሚገኘው በአዲሱ የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ግቢ ውስጥ እየተካሄደ ይገኛል።

ለተጨማሪው: @EventAddis1
ልዑል እና ሚኪ የተጣመሩበት "ልዑል" ኮንሰርት

ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ እና ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ የተጣመሩበት "ልዑል" ኮንሰርት የፊታችን ሰኔ 1 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል። ከሁለቱ ድምጻዊያን በተጨማሪም ድምጻዊ ሳሚ ዳን በኮንሰርቱ ስራውን ያቀርባል ተብሏል ።

ወጣቱ ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ ከወራት በፊት "ልዑል" የተሰኘ አልበም ለአድማጮች ያደረሰ ሲሆን በሌላ በኩል ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ ከዓመታት በኃላ በቅርቡ የሙዚቃ አልበሙን ለአድማጮች ያደርሳል ተብሏል።

ለተጨማሪው: @EventAddis1
የድምፃዊት እግቱ ጉዳይ ከምን ደረሰ?

ድምፃዊት ትዕግስት ኃይሉ (እግቱ) የደረሰባትን በፋስት መረጃ ካደረስን በኋላ በርካታ ጥያቄዎች ተነስቷል። ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ከትራንስፖርት ቢሮ፣ ከባህል እና ቱሪዝም ቢሮ መረጃውን ከተመለከቱ በኋላ ነገሩን ለማጣራት ተደውሎልን ነበር ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ ላደረጋችሁት ተነሳሽነት ፋስት መረጃ ከልብ ያመሰግናል።

እግቱ ምን ደረጃ እንደደረሰች ፋስት መረጃ ድምፃዊቷን ለማውራት ሞክረን ነበር ከፈረስ ጋር እየተነጋገርኩ ነው የደረስኩበትን ነገር አሳውቃለሁ ብላን ነበር።

አሁን ማምሻውን የደረሰችበትን ነገር አሳውቃናለች።

ሙከራውን አምልጣ ቤት እንደገባች መጀመሪያ ወደ ፈረስ ትራንስፖርት ደውላ የደረሰባን ስትነግራቸው ስትሳፈር ኪሎሜትር ስላላስጀመረች ኤቪደንስ ስለሌለ ነገሩን አክብዶታል ብላለች። (መጀመሪያ ከቤት ሲወስዳት በፈረስ ነበር ደውላ የጠራችው ስትመለስ ግን አላስጀመረችም ነበር።)

ከዛ በኋላስ ምን ተፈጠረ?
ፈረስ ትራንስፖርት እና ድምፃዊቷ በአሁኑ ወቅት በመነጋገር አሽከርካሪው ከስራው እንደታገደ እግቱ ለፋስት መረጃ ገልፃለች፣ አሽከርካሪውም ደውሎ እንዳወሩ እና መጀመሪያ ማመን አልፈለገም ነበር ጉዳዩ ሲሪየስ መሆኑን ሲያውቅ ይቅርታ ጠይቆኛል ብላለች።

እኔ ዋና አላማዬ ከእኔ ስህተት ብዙ ሰው እንዲማር ነበር ይፋ ያደረኩት ብላለች። ኮሜንቶቹን በተመለከተ እኔን በመተባበር እንኳን አተረፈሽ ያሉ በርካታ ሰዎች ከልብ አመስግናለሁ። እኔ አሁን በጣም ደህና ነኝ ብላለች።

በጣም የሚያሳዝን ከሰው የማይጠበቅ ሰው እንዴት ሰው ላይ እንደዚህ ይመኛል የሚያስብሉ ኮሜንቶችን ተመልክቻለሁ፣ ሌሎች ሰዎች የደረሰባቸውን ወጥተው እንዳይናገሩ የሚያደርግ ነው፣ በራቸውን የዘጉ ብዙ ነገር የሆኑ አሉ ለእነሱ እንደዚህ መባሉ ጥሩ አይደለም። እኔ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም በማለት አስተያየት ሰጪዎችን በተመለከተ ሃሳቧን ተናግራለች።

📍መረጃው የፋስት መረጃ ነው

ለተጨማሪው: @EventAddis1
የሳምንቱን የሙዚቃ ሰሞነኛ መረጃዎች ( በአጭሩ )

📍ሙዚቃ

- ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ እና ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ  የተጣመሩበት "ልዑል" ኮንሰርት የፊታችን ሰኔ 1 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል። ከሁለቱ ድምጻዊያን በተጨማሪም ድምጻዊ ሳሚ ዳን በኮንሰርቱ ስራውን ያቀርባል ተብሏል።

-የድምጻዊ ጉቱ አበራ "lyolee" የተሰኘ የኦሮምኛ ነጠላ ሙዚቃ ቪዲዮ ዛሬ አርብ ግንቦት 23 2016 ዓ.ም በድምጻዊው የዩቲዩብ ቻናል ይለቀቃል። የሙዚቃው ግጥም እና ዜማ በራሱ በድምጻዊው ጉቱ አበራ ተሰርቷል።

-የወጣቷ ድምፃዊት አዲስ ጌራ "መስከረሜ" የተሰኘ አዲስ ነጠላ ሙዚቃዋ ዛሬ አርብ ግንቦት 23 አርብ ማታ 2016 ዓ.ም በአዲስ ጌራ ዩቲውብ ቻናል እና ዓለምአቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያዎች ላይ ይለቀቃል። የሙዚቃው ግጥምና ዜማው የአዲስ ጌራ እና የህዝብ ሲሆን ሙዚቃ ቅንብሩን አብርሀም ኪዳኔ ሲሰራው ሙሳ ማቲ ሚክስና ማስተር አድርጎታል ፤ ልዋም መሀሪ በቤዝ ጊታር ፣ ዘሪሁን በለጠ በሳክስፎን ተሳትፈውበታል።

-የድምጻዊ ወንዲ ማክ አዲስ አልበም በቅርቡ ለአድማጮች ይደርሳል። ድምፃዊ ወንደሰን መኮንን በመድረክ ስሙ (ወንዲ ማክ) በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፁም "ፈጣሪ ፈቅዶ እነሆ በአዲስ አልበም መጥተናል በቅርብ ቀን ይጠብቁን" ብሏል።

-የሮፍናን ኑሪ "ሮፍናን ማስተር ክላስ" በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል። ይህ ዝግጅት ሙዚቀኛው የሙዚቃ ዕውቀቱን መሰረት አድርጎ ከባለሙያ ስነምግባር እስከ የራስን ብራንድ ፈጠራ ድረስ ያለውን ልምድ የሚያካፍልበት ነው።

-አንጋፋዋ ድምጻዊት ማሪቱ ለገሠ ነገ ግንቦት 24 2016 ዓ.ም በቶቶት የባህል ምግብ አዳራሽ ከምሽቱ 1:00 ጀምሮ የሙዚቃ ስራዋን ታቀርባለች።

📍መረጃውን ሲጠቀሙ ምንጭ ይጠቀሱ !

ለተጨማሪው: @EventAddis1
5ኛው ዙር የተስፋ አዲስ ቤተሰቦች የደም ልገሳ

5ኛው ዙር የተስፋ አዲስ ቤተሰቦች የደም ልገሳ መርሃግብር ከተለያዩ ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በሀገራችን በ12 ከተሞች በዚህ ሳምንት መጨረሻ ግንቦት 24 እና 25 2016 ዓ.ም  ይካሄዳል።

እነዚህም ከተሞች አርባምንጭ ፣ጎንደር ፣አዳማ ፣መቀሌ ፣ሐዋሳ ፣ጅማ ፣ባህርዳር ፣ድሬዳዋ ፣ጂንካ ፣ሀላባ ፣ሐረር ፣እና መዲናችን አዲስ አበባ ናቸው።

የፕሮግራሙ አስተባባሪ ማስተዋል እያሱ "ከተጠቀሱት ከተሞች በተጨማሪ በሌሎችም ከተሞች ያሉ በጎ ፍቃደኞች ወደ ደም ባንኮች ጎራ ብለው በዕለቱ አብረው ደም ቢለግሱ ደስ ይለናል" ስትል ለኤቨንት አዲስ ድረገፅ ተናግራለች።

በተጨማሪም" ኑ በደማች አዲስ ታሪክ እንስራ። በሚተካው ደም የማይተካውን የሰው ልጅ ህይወት እናድን። ለካንሰር ታማሚ ህፃናት የነገን የማየት ተስፋ ምክንያት እንሁን ።" ብለዋል አዘጋጆቹ ።

ለተጨማሪው: @EventAddis1
የሳምንቱ ጥበባዊ ውይይቶችን (በአጭሩ )

📍ጥበባዊ ውይይቶች

- በዋልያ መጻህፍት የሚዘጋጀው ከደራስያን ጋር የመጨዋወት እና መጽሐፍ የማስፈረም ልዩ ሥነሥርዓት በዚህ ሳምንት "በኢትዮጵያ የውርስ ሕግ መሰረት ሀሳቦች " የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ነገ ቅዳሜ ግንቦት 24 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ጀምሮ በዋልያ መጻሕፍት ውይይት ይካሄዳል።በዕለቱም የሕግ ባለሞያው ዳዊት በዛብህ ያወያያል።

- በዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ት/ቤት በየሳምንቱ የሚዘጋጀው የሀሳብ ውይይት በዚህም ሳምንት "ነገረ እኩይ" የተሰኘ ርዕስ መርጧል ይህም ውይይት  ቅዳሜ ግንቦት 27 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ 5 ኪሎ በሚገኘው አፄ ናኦድ ት/ቤት ግቢ ውስጥ ይካሄዳል።"ነገረ እኩይ"በሚል ርዕስ በዮናስ ዘውዴ  መነሻ ሀሳብ ይቀርባል ተብሏል።

-የብራና ጁፒተር የንባብ ቡድን ነገ ቅዳሜ ግንቦት 24  2016 ዓ.ም በዶ/ር መላኩ አዳል "ለሉሲ ሀገር ሰዎች" መጽሐፍ ላይ ውይይት ያካሄዳል። ይህ ውይይት ከ9:45 እስከ 12:00 ካዛንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ውስጥ ይካሄዳል።

-በ"አስተውሎት" ፊልም ላይ ነገ ቅዳሜ ግንቦት 24 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ውስጥ ሙያዊ ውይይት ይካሄዳል። በፊልሙ ላይ ሰውመሆን ይስማው ፣ ቴዎድሮስ አበበ ፣ ሚካኤል ሚሊዮን ሀሳብ አቅራቢ ባለሞያዎች ናቸው።

- "ስብሐቲዝም" የሀሳብ ውይይት የፊታችን እሁድ ግንቦት 25 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት(ወመዘክር) አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል። በዚህኛው ዙር "ስለ አርምሞ እንነጋገር " የተሰኘ ርዕሰ ጉዳይ የተመረጠ ሲሆን በኤልያስ አእምሮ (ዶ/ር) መነሻ ሀሳብ ይቀርባል ተብሏል።

📍መረጃውን ሲጠቀሙ ምንጭ ይጠቀሱ !

ለተጨማሪው: @EventAddis1
"ኢትዮ የምግብና መጠጥ ፌስቲቫል"

"ኢትዮ የምግብና መጠጥ ፌስቲቫል" ከሰኔ 5 እስከ 9 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል።

ለ5 ተከታታይ ቀናት በሚቆየው "ኢትዮ የምግብና መጠጥ ፌስቲቫል" በምግብ፣ በመጠጥ፣ በፓኬጂንግ እና ተዛማጅ መስኮች ላይ የተሰማሩ ግብዓት አቅራቢዎች፣ አምራቾች፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ ከዘርፉ ጋር የተገናኙ አምራች እና አስመጪዎች እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት ይሳተፋሉ ተብሏል።

በፌስቲቫሉ ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም፣ ሽልማት የሚያስገኙ ልዩ ልዩ ውድድሮች እና የመዝናኛ ፕሮግራሞች መካተታቸው ተገልጿል።

አዘጋጆቹ "ኢትዮ የምግብና መጠጥ ፌስቲቫል" በተሳካ መልኩ ይካሄድ ዘንድ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምዝገባ እያደረጉ መሆናቸውን ያስታወቁ እስካሁን ያልተመዘገቡ ተቋማትም በቀሩት አጭር ቀናት ምዝገባ አድርገው ይህን ፌስቲቫል እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህን የምግብና መጠጥ ፌስቲቫል ለመታደም ለሚፈልጉ ጎብኚዎች መግቢያው በነፃ ነው ተብሏል።

ፌስቲቫሉ የኢንዱስትሪውን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማገናኘትና በማስተሳሰር ረገድ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

ፌስቲቫሉን በአምራች ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት የምግብና መጠጥ ምርምርና ልማት ማዕከል ፣አሜዚንግ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ ፣ ዳብ ትሬዲንግ በጋራ በመሆን አዘጋጅተዋል።

ለተጨማሪው: https://news.1rj.ru/str/EventAddis1